ቀጥታ፡

መንግስት የሰጠው ትኩረት የዩኒቨርሲቲውን የኒውክለር ሪአክተር ልህቀት ማዕከል ለማጠናከር ጉልህ ሚና አለው

አዲስ አበባ፤ጥቅምት 25/2018(ኢዜአ)፦መንግስት ለኒውክለር ኃይል የሰጠው ትኩረት የዩኒቨርሲቲውን የኒውክለር ሪአክተር ልህቀት ማዕከል ለማጠናከር ጉልህ ሚና እንዳለው የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ገለጸ።

ዩኒቨርሲቲው ሀገሪቱ በኒውክለር ኃይል ልማት የያዘችውን እቅድ ለማሳካት በዘርፉ ምርምሮችን ለማካሄድ እና የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት በትኩረት እየሰራ መሆኑንም አስታውቋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ምረቃ ላይ በ30 ቢሊየን ዶላር እንደሚገነቡ ካበሰሯቸው ፕሮጀክቶች መካከል የኒውክለር ፕላንት አንዱ ነው።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ጥቅምት 4 ቀን 2018 ዓ.ም ባካሄደው 49ኛ መደበኛ ስብሰባው የኢትዮጵያ ኒውክሌር ኃይል ኮሚሽን ማቋቋሚያ ደንብ ላይ ውሳኔ ያሳለፈ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኮሚሽኑን ኮሚሽነር መሾማቸው ይታወቃል።

የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዝዳንቶች ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ኒውክለር ኃይል ከንፁህ የኃይል አማራጮች አንዱና ለተለያዩ ተግባራት ጥቅም መስጠት የሚያስችል ነው።

በዩኒቨርሲቲው የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዝዳንት አብርሃም ደበበ (ዶ/ር) እንዳሉት፥ ዩኒቨርሲቲው ካሉት ስምንት የልህቀት ማዕከላት የኒውክለር ሪአክተር ቴክኖሎጂ አንዱ ነው።

በዚህም ዩኒቨርሲቲው ባለፉት ስምንት ዓመታት በዘርፉ ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰው፤ ከ2016 ዓ.ም ጀምሮ ተማሪዎችን በማስተርስ መርሃ ግብር እያስተማረ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የዩኒቨርሲቲው የኒውክለር ሪአክተር ቴክኖሎጂ ልህቀት ማዕከል ህንፃ ግንባታ መጠናቀቁንም ገልፀዋል።

የኒውክለር ፕላንት ለመገንባት መታቀዱና የኢትዮጵያ ኒውክሌር ኃይል ኮሚሽን መቋቋም ዩኒቨርሲቲው እያከናወነ ላለው ተግባር ተጨማሪ አቅም የሚፈጥር መሆኑን አስረድተዋል።

በዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ከማል ኢብራሂም (ዶ/ር) በበኩላቸው፥ የኒውክለር ፕላንት አማራጭ ሀይል ለማግኘት ጠቀሜታ እንዳለው አስታውቀዋል።

ዩኒቨርሲቲው የኒውክለር ሃይል ለሰላማዊ አገልግሎት ያለውን አስፈላጊነት በመረዳት ከስምንት ዓመት በፊት የኒውክለር ሪአክተር ቴክኖሎጂ ልህቀት ማዕከል ማቋቋሙን ተናግረዋል።

የልህቀት ማዕከሉ ህንፃ ግንባታ መጠናቀቁን ገልፀው፥ የላቦራቶሪ ዕቃዎችን ለማሟላት ከሚመለከተው አካል ጋር እየተሰራ ነው ብለዋል።

መንግስት ለኒውክለር ሀይል የሰጠው ትኩረት ዩኒቨርሲቲው የጀመረውን ጥረት እንደሚያጠናክር የገለፁት ደግሞ የዩኒቨርሲቲው የአስተዳደር ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ተመስገን ወንድሙ ናቸው።

ዩኒቨርሲቲው ለኢትዮጵያ ኒውክሌር ኃይል ኮሚሽን አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑንም ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም