ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ቀይ ባሕርን እንዳትጠቀም የሚከለክል ሕግ የለም

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 25/2018 (ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ ቀይ ባሕርን እንዳትጠቀም የሚከለክል ሕግ እስከሌለ ድረስ ቀይ ባሕርን ለመጠቀም ጥያቄ ማንሳቷ ሕጋዊ መሠረት እንዳለው ተገለጸ።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህርና ተመራማሪ ኪዳኔ ደያሳ፤ ኢትዮጵያ የባሕር በር ለማግኘት እያደረገች ያለውን ሂደት ከሕግ አንጻር በቅርብ እንደሚከታተሉ አንስተዋል።

በዚህም መሠረት የባሕር በር አልባ የተደረገችው ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የባሕር ሕግ የባሕር መዳረሻ የማግኘት መብት እንዳላት ጠቁመው፤ ኢትዮጵያ ቀይ በሕርን እንዳትጠቀም የሚከለክል ሕግ የለም ብለዋል።

ኢትዮጵያ ስትጠቀምበት የነበረው አሰብ ወደብ በአልጀርስ ስምምነት ላይ እንኳን ምን መሆን እንዳለበት በግልጽ የተገለጸ ነገር አለመኖሩንም አስረድተዋል።

የአልጀርስ ስምምነት ሲፈረምም ሀገራቱ ይገባኛል በሚሉት ድንበር ላይ ብቻ ማተኮሩን አውስተዋል።

ስለዚህ አሰብ ወደብንና ቀይ ባሕርን ኤርትራ የኔ ብላ እንድትጠቀምና ኢትዮጵያ አንዳትጠቀም ተብላ እንድትከለከል የሚያደርግ ሕጋዊ መሠረት አለመኖሩን ነው ያረጋገጡት።

በሌላ በኩል ከዓለም አቀፍ ንግድ በተጨማሪ በዓለም አቀፍ የባሕር ሕግ ከፍተኛ ባሕር የሚባል የሁሉም የሆነ ሀብት መባሉን ጠቁመው፤ ይህን ሃብት ለመጠቀም የባሕር በር የግድ ያስፈልጋል ብለዋል።

ስለዚህ ኢትዮጵያ በዚህ አማራጭም ቀይ ባሕርን የመጠቀም መብት እንዳላት መዘንጋት የለበትም ነው ያሉት።

በአጠቃላይ ከላይ በተገለጹት መነሻዎች መሠረት ኢትዮጵያ የባሕር በር ለማግኘት ያነሳችው ጥያቄ ዓለም አቀፍ ሕጋዊ መሠረት እንዳለው በአጽንኦት ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ስትጠቀምበት የነበረው አሰብ ወደብና ቀይ ባሕር ወደ ኤርትራ እንዲጠቃለል የተደረገበት አግባብን የሚያሳይ ማስረጃ አለመገኘቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቅርቡ በተካሄደው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ ላይ መናገራቸው ትክክል መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ካለችበት የኢኮኖሚ፣ የሕዝብ ቁጥርና ዘርፈ-ብዙ ዕድገት አኳያ ለወጪና ገቢ ንግድ የባሕር በር እንደሚያስፈልጋት ነው ያስረዱት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም