በሻምፒዮንስ ሊጉ ፒኤስጂ ከባየርሙኒክ እና ሊቨርፑል ከሪያል ማድሪድ የሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ይጠበቃሉ - ኢዜአ አማርኛ
በሻምፒዮንስ ሊጉ ፒኤስጂ ከባየርሙኒክ እና ሊቨርፑል ከሪያል ማድሪድ የሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ይጠበቃሉ
አዲስ አበባ፤ጥቅምት 25/2018 (ኢዜአ)፦ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የአራተኛ ዙር መርሃ ግብር ከዛሬ ጀምሮ ይካሄዳል።
የወቅቱ የውድድሩ አሸናፊ ፒኤስጂ ከባየርሙኒክ ምሽት 5 ሰዓት ላይ በፓርክ ደ ፕሪንስ ስታዲየም የሚያደርጉት ጨዋታ የዓለምን ትኩረት ስቧል።
ፒኤስጂ እና ባየርሙኒክ ዘንድሮ ባደረጓቸው ሶስት የሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታዎች በተመሳሳይ ዘጠኝ ነጥብ በማግኘት በግብ ክፍያ ተበላልጠው አንደኛና ሁለተኛ ደረጃን ይዘዋል።
ሁለቱ ቡድኖች በአውሮፓ መድረክ ሲገናኙ ለ15ኛ ጊዜ ነው።
ከዚህ ቀደም ባደረጓቸው 14 ጨዋታዎች ፒኤስጂ ስምንት ጊዜ ሲያሸንፍ ሙኒክ ስድስት ጊዜ ድል ቀንቶታል።
ቡድኖች እ.አ.አ በ2019/20 በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ፍጻሜ ተገናኝተው ባየር ሙኒክ 1 ለ 0 ያሸነፈበት አጋጣሚ በእርስ በእርስ ግንኙነታቸው ውስጥ በዋናነት የሚጠቀስ ነው።
በውድድር ዓመቱ ያደረጋቸውን 15 ጨዋታዎች ያሸነፈው ባየር ሙኒክ ዛሬ ከፒኤስጂ ጥልቅ ፈተና ይጠብቀዋል። የጀርመኑ ቡድን የስድስት ጊዜ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ አሸናፊ ነው።
የ43 ዓመቱ ጣልያናዊ ዳኛ ማውሪዚዮ ማሪያኒ ተጠባቂውን ጨዋታ በዋና ዳኝነት ይመሩታል።
ምሽት 5 ሰዓት ላይ በአንፊልድ ሮድ ስታዲየም ሊቨርፑል ከሪያል ማድሪድ የሚያደርጉት ጨዋታም ተጠባቂ ነው።
በሻምፒዮንስ ሊጉ በስድስት ነጥብ 10ኛ፣ ሪያል ማድሪድ በዘጠኝ ነጥብ አምስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።
ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ 12 ጊዜ ተገናኝተው ሊቨርፑል ሰባት ጊዜ ሲያሸንፍ ሪያል ማድሪድ አራት ጊዜ አሸንፏል። አንድ ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።
ቡድኖቹ በሶስት ፍጻሜዎች ላይ ተገናኝተው ሪያል ማድሪድ ሁለት ጊዜ ሲያሸንፍ ሊቨርፑል አንድ ጊዜ ድል ቀንቶታል።
ባለፈው የውድድር ዓመት በሻምፒዮንስ ሊጉ ተገናኝተው ሊቨርፑል 2 ለ 0 ማሸነፉ አይዘነጋም።
ሊቨርፑል የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን ስድስት ጊዜ ሲያነሳ ማድሪድ 15 ጊዜ በማሸነፍ የውድድሩ ስኬታማ ክለብ ነው።
በክረምቱ የዝውውር መስኮት ከሊቨርፑል ወደ ሪያል ማድሪድ በነጻ ዝውውር ያመራው ትሬንት አሌክሳንደር አርኖልድ የቀድሞ ክለቡን ለመግጠም ወደ መርሲሳይድ አምርቷል።
የ41 ዓመቱ ሮማኒያዊ ስቴቫን ኮቫክስ ጨዋታውን በዋና ዳኝነት ይመሩታል።
በሌሎች መርሃ ግብሮች ጁቬንቱስ ከስፖርቲንግ ሊዝበን፣ ቶተንሃም ሆትስፐርስ ከኤፍሲ ኮፐንሃገን፣ አትሌቲኮ ማድሪድ ከዩኒየን ሴንት ጂሎይስ፣ ኦሎምፒያኮስ ፒኤስቪ አይንድሆቨን እና ቦዶ ግሊምት ከሞናኮ በተመሳሳይ ከምሽቱ 5 ሰዓት ላይ ጨዋታቻውን ያደርጋሉ።
ምሽት 2 ሰዓት ከ45 ላይ ስላቪያ ፕራግ ከአርሰናል እና ናፖሊ ከኢንትራክት ፍራንክፈርት ይጫወታሉ።