ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የንግድ እና የኢንቨስትመንት ምህዳሩን የበለጠ ለማጠናከር በቁርጠኝነት እየሰራች ነው - ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 24/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የንግድ እና የኢንቨስትመንት ስራ ምቹነት የበለጠ ለማሻሻል በቁርጠኝነት እየሰራች እንደምትገኝ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር) ገለጹ።

የኢትዮጵያ እና የአውሮፓ ህብረት ኢንቨስትመንት ፎረም ዛሬ በፈረንሳይ ፓሪስ ተጀምሯል።

በውይይቱ ላይ የተሳተፉ ባለድርሻ አካላት ኢትዮጵያ የንግድ ስራ ምቹነትን ለማሻሻል እና ዘላቂ ኢንቨስትመንት የበለጠ ለመሳብ ያላትን ጠንካራ ቁርጠኝነት አንስተዋል።

የመንግስት ተወካዮች እና ዓለም አቀፍ አጋሮች የአሰራር ስርዓቶችን ቀልጣፋ ማድረግ፣ ተጠያቂነትን ማስፈን እና የመንግስት-የግል ምክክርን ማጠናከር ለተወዳዳሪነት እና ስራ ፈጠራ ቁልፍ ጉዳዮች መሆናቸውን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን በማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙ አማካኝነት የኢትዮጵያን የንግድ ስራ ምቹነት ለማሻሻል ያለውን ቁርጠኝነት በስብስባው ላይ ገልጿል።


 

የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር) ኢትዮጵያ የንግስ ስራ ምቹነትን ለማሻሻል ረጅም ርቀት መሄዷን ገልጸው ለኢንቨስትመንት እና ስራ ፈጠራ የሚሆን ምቹ ምህዳርን ለመፍጠርም ጥረቶች እየተደረጉ ነው ብለዋል።

የጀርመን ዓለም አቀፍ የልማት ትብብር ድርጅት(ጂአይዜድ) የኢትዮጵያ አጋሮች የንግድ ምህዳሩን የበለጠ ምቹ ለማድረግ እያደረጉ ያለውን ድጋፍ ያደነቀ ሲሆን ዘላቂ ውጤት ለማምጣት ትብብርን የበለጠ ማጠናከር እንደሚገባ አመልክቷል።

በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር የኢኮኖሚ አማካሪ ክርስቶፍ ሞርቾይን ከኢንቨስትመንት ከባቢ ጋር በተገናኘ የተቋቋመው የጋራ ትብብር ቡድን ለሌሎች ምሳሌ የሚሆን ማዕቀፍ ነው ብለዋል።

ቡድኑ የመንግስት እና የግሉ ዘርፍ ያላቸውን ትስስር ለማጠናከር እንደሚያስችልም አመልክተዋል።

በውይይቱ ላይ ኢትዮጵያና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት የሪፎርሙን ትግበራ ለመቀጠል እንዲሁም ከግሉ ዘርፍና የልማት አጋሮች ጋራ ያለውን ትብብር በማጠናከር የኢትዮጵያን ሁሉን አቀፍና ዘላቂ የልማት ግቦች እንዲሳካ በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ መግለጻቸውን የገንዘብ ሚኒስቴር ለኢዜአ በላከው መረጃ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም