ቀጥታ፡

ግማሽ ክፍለ ዘመን ያስቆጠረው የኢትዮጵያ እና አውሮፓ ህብረት አጋርነት

ግማሽ ክፍለ ዘመን ያስቆጠረው የኢትዮጵያ እና አውሮፓ ህብረት አጋርነት

ኢትዮጵያ እና አውሮፓ ያላቸው ታሪካዊ ወዳጅነት በርካታ ክፍለ ዘመናትን ያስቆጠረ ነው።

የሁለቱ ወገኖች ግንኙነት በአራተኛው ክፍለ ዘመን እንደጀመረ መረጃዎች ያመለክታሉ። በአክሱም ንጉስ ኢዛና ወቅት ኢትዮጵያ ከምስራቅ ሮም መንግስት ጋር ዲፕሎማሲያዊ እና ሃይማኖታዊ ግንኙነት እንደነበራት ይነገራል።

15ኛው ክፍለ ዘመን የመጀመሪያው በሰነድ የተደገፈ የኢትዮጵያ እና አውሮፓ የዲፕሎማሲ ተልዕኮ ግንኙነቶች የተደረጉበት ወቅት ነው።

እ.አ.አ በ1441 የኢትዮጵያ ልዑክ በሮማ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ምክር ቤት (The Council of Florence) ስብስባ ላይ ተሳትፎ ያደረገ ሲሆን ከሰሃራ በታች በሚገኙ ሀገራት እና አውሮፓ መካከል የተደረገ የመጀመሪያው ግንኙነት እንደሆነ ታሪክ ያወሳል።

በወቅቱ የኢትዮጵያ ልዑካን ወደ ሮም፣ ቬኒስ እና ሊዝበን ጉብኝቶችን አድርገዋል።

ከዛ በኋላ ባሉ ክፍለ ዘመናት በኢትዮጵያ እና አውሮፓ ሀገራት መካከል በርካታ የዲፕሎማሲ ተልዕኮ እንቅስቃሴዎች እና የጉብኝት ልውውጦች ተደርገዋል።

እ.አ.አ 1975 ኢትዮጵያ ከአውሮፓ ማህበረሰብ ጋር ዘመናዊ የዲፕሎማሲ ግንኙነት የጀመረችበት ጊዜ ነው።

ኢትዮጵያ እና የአውሮፓ ህብረት (በቀድሞ አጠራሩ የአውሮፓ ኢኮኖሚ ማህበረሰብ) እ.አ.አ ፌብሩዋሪ 28 1975 በቶጎ ሎሜ የትብብር ስምምነት ተፈራረሙ። ስምምነቱ የሎሜ ድንጋጌ እየተባለ ይጠራል።

ስምምነቱ ለኢትዮጵያ እና ለአውሮፓ ህብረት ትብብር መሰረት የጣለ ታሪካዊ ሁነት ነው።

የኢኮኖሚ ልማት፣ የንግድ ትብብር፣ የልማት ድጋፍ እና የወጪ ንግድ የስምምነቱ አበይት ማዕቀፎች ናቸው።

የሎሜ ስምምነት አራት ጊዜ ማሻሻያ ተደርጎበታል። ማሻሻያዎቹ ኢትዮጵያ እና የአውሮፓ ህብረት በፖለቲካ፣ ዴሞክራሲ፣ ኢንዱስትሪ፣ አካባቢ ጥበቃ እና ቀጣናዊ ትስስርን ጨምሮ ሁለቱ ወገኖች ያላቸውን የትብብር አድማስ ማስፋትን ያለሙ ናቸው።

እ.አ.አ በ2000 የሎሜ ስምምነት ወደ ኮቶኑ ስምምነት ተሸጋገረ። ኢትዮጵያ እና የአውሮፓ ህብረት በቤኒን ኮቶኑ አዲስ የትብብር ማዕቀፍ ተፈራረሙ።

የኮቶኑ ስምምነት የሁለቱን ወገኖች አጋርነት ያስቀጠለ ነው። የፖለቲካ ምክክሮች፣ ሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ እና ኢኮኖሚያዊ ስምምነቶች አካቷል።

ስምምነቱ ሁለት ጊዜ ማሻሻያዎች የተደረጉበት ሲሆን እ.አ.አ በ2020 ማዕቀፉ እስከ እ.አ.አ 2024 እንዲቀጥል ተወስኗል።

እ.አ.አ በ2023 በሶሞአ በተደረገ ውይይት የድህረ ኮቱኑ ስምምነት የተባለለት ማዕቀፍ በአፍሪካ ህብረት እና አውሮፓ ህብረት መካከል ተፈርሟል።ኢትዮጵያ የዚህ ስምምነት ተጠቃሚ ናት።

እ.አ.አ በ2016 የተፈረመው የኢትዮጵያ እና የአውሮፓ ህብረት ስትራቴጂካ ትስስር ማዕቀፍ ስምምነት የበለጠ ስትራቴጂካዊ አጋርነትን ያጸና ነው።

የአውሮፓ ህብረት ያቋቋመው የአውሮፓ ቡድን በኢትዮጵያ (Team Europe in Ethiopia) ህብረቱን፣ የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ እና 21 የህብረቱ አባል ሀገራትን አቅፎ የያዘ ነው።

ከአውሮፓ ህብረት 27 አባል ሀገራት መካከል 21ዱ በኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ተልዕኮ ውክልና አላቸው።

ኢትዮጵያ እና የአውሮፓ ህብረት ሰላም እና ፀጥታ፣ የምግብ ስርዓት፣ ዘላቂ ኢነርጂ ልማት፣ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን፣ የግሉ ዘርፍ ልማት እና ትራንስፖርት ጨምሮ በሌሎች መስኮች ትብብር አላቸው።

የአውሮፓ ህብረት በኮቶኑ ስምምነት የነበረውን የአውሮፓ የልማት ፈንድ ድጋፍ በመተካት ከእ.አ.አ 2021 እስከ 2027 የሚቆይ የፋይናንስ ማዕቀፍ እየተገበረ ይገኛል።

629 ሚሊዮን ዩሮ ፈሰስ የሚደረግበት ይህ ማዕቀፍ ከአውሮፓ ህብረት ተቋማት እና አባል ሀገራት አስተዋጽኦ የሚገኝ ሲሆን በየዓመቱ በኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች ለሚከናወኑ ስራዎች የሚውል ነው።

ታዳሽ ኢነርጂ፣ ዲጂታላይዜሽን፣ ዘላቂ የስርዓተ ምግብ ግንባታ፣ ትራንስፖርት፣ የሰው ሀብት ልማት፣ የፍልሰት አስተዳደር እና ሰላም ግንባታ ድጋፍ የሚደረግባቸአው መስኮች ናቸው።

ባለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ እና በአውሮፓ ህብረት ትብብር ውስጥ የሚጠቀሱ አንኳር ጉዳዮች አሉ።

ከቅርቡ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ በመስከረም ወር 2018 ዓ.ም ወደ ቤልጂየም ብራሰልስ በማምራት ከአውሮፓ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ቮን ደር ሌይን ጋር የሁለትዮሽ ውይይት አድርገዋል።

ሁለቱ መሪዎች ኢትዮጵያ እና የአውሮፓ ህብረት የጋራ ፍላጎታቸውን መሰረት አድርገው ግንኙነታቸውን የበለጠ ለማጠናከርና ለማስፋት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ መክረዋል።

ከውይይቱ ጎን ለጎን ኢትዮጵያ እና የአውሮፓ ህብረት ግሎባል ጌትዌይ ፓርትነርሺፕ" የትብብር ስምምነት ተፈራርመዋል።

"ግሎባል ጌትዌይ ፓርትነርሺፕ" በአውሮፓ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ቮን ደር ሌይን የሚመራ የአውሮፓ ህብረት ዓለም አቀፍ ኢኒሼቲቭ ሲሆን ህብረቱ ከተለያዩ ሀገራት በዲጂታላይዜሽን፣ በታዳሽ ኃይል፣ በስርዓተ ምግብ፣ በጤና፣ በዘላቂ ግብርና፣ በሰላም እና ደህንነትን ጨምሮ በቁልፍ ዘርፎች ያለውን ትብብር እና የኢንቨስትመንት ግንኙነት ለማጠናከር ያለመ ነው።

ስምምነቱ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ ያስቆጠረውን የኢትዮጵያ እና የአውሮፓ ህብረት የዲፕሎማሲ ትስስር ወደ ላቀ ደረጃ የሚያደርስ ትልቅ እርምጃ መሆኑን ፕሬዝዳንት ታዬ ገልጸዋል።

በተጨማሪም ስምምነቱ ሁለቱ ወገኖች እ.አ.አ በ2016 ለተፈራረሙት የስትራቴጂክ ትስስር የጋራ ድንጋጌ አዲስ አቅም እንደሚፈጥርም ተመላክቷል።

ኢትዮጵያ እና የአውሮፓ ህብረት ባለፈው ሳምንት ለ2025 ዓመታዊ የድርጊት መርሃ ግብር የ90 ሚሊዮን ዩሮ የፋይናንስ ስምምነት በአዲስ አበባ መፈራረማቸው የሚታወስ ነው።

በአሜሪካ ዋሺንግተን ዲሲ በመስከረም ወር 2018 ዓ.ም የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) እና የዓለም ባንክ ዓመታዊ ስብስባ ላይ የተሳተፉት የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አሕመድ ሽዴ ከስበሰባው ጎን ለጎን ከአውሮፓ የኢንቨስትመንት ባንክ ከዓለም አቀፍ አጋርነት ዳይሬክተር ቱራያ ትሪኪ ጋር መክረው ነበር።

በወቅቱ የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ ለገጠር ፋይናንስ አቅርቦት ማሻሻያ ፕሮግራም (RUFIP III) ሶስተኛ ምዕራፍ ማስፈጸሚያ የሚውል የ110 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ለማድረግ ቃል መግባቱ የሚታወስ ነው።

ስምምነቱን የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ሰመሪታ ሰዋሰው እና በኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት አምባሳደር ሶፊ ፍሮም ኢመስበርገር ተፈራርመውታል።

ኢትዮጵያ እና የአውሮፓ ህብረት የ240 ሚሊየን ዩሮ የድጋፍ ስምምነት በመጋቢት ወር 2017 ዓ.ም ተፈራርመዋል።

ድጋፉ የአውሮፓ ህብረት የኢትዮጵያን ልማት በተለያዩ ወሳኝ ዘርፎች ለማጠናከር የሚውል ነው።

ኢትዮጵያ እና የአውሮፓ ህብረት በታህሳስ ወር 2017 ዓ.ም የጋራ ምክክር በአዲስ አበባ ያደረጉ ሲሆን በውይይቱ የጋራ አጋርነታቸውን የበለጠ ለማጠናከር ተስማምተዋል።

ሁለቱ ወገኖች በህዳር ወር 2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ ተመሳሳይ የጋራ የምክክር መድረክ ማድረጋቸው አይዘነጋም።

በ2011 ዓ.ም ኢትዮጵያ እና አውሮፓ ህብረት በጤና ዘርፍ እና የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦት ላይ ያተኮረ የ20 ሚሊዮን ዩሮ የድጋፍ ስምምነት ተፈራርመዋል።

ዲፕሎማሲያዊ ትስስሩ ሁለቱ ወገኖች በሰኔ ወር 2008 ዓ.ም ከተፈራረሙት የስትራቴጂክ የጋራ ድንጋጌ በኋላ የበለጠ እየተጠናከረ መጥቷል።

ዛሬ በፈረንሳይ ፓሪስ የተካሄደው የኢትዮጵያ እና የአውሮፓ ህብረት ኢንቨስትመንት ፎረሙ የሁለቱን አካላት ግንኙነት ለማጠናከር እና ቀጣይነት ያለው ዕድገት ለማረጋገጥ ወሳኝ ሚና የሚጫወት ነው።

በፎረሙ ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ(ዶ/ር)፣ የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ፣ የአውሮፓ ኮሚሽን የአፍሪካ ተጠባባቂ ዳይሬክተር ጌዛ ስትራመር፣ የፈረንሳይ የወጪ ንግድ እና ኢኮኖሚ ሚኒስቴር መልዕክተኛ ኒኮላስ ፎርሲየር፣ የሜዴፍ ኢንተርናሽናል ምክትል ፕሬዝዳንት ፋብሪስ ላሳች፣ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት፣ ባለሀብቶች እና የንግድ መሪዎች ተገኝተዋል።

ፎረሙ በኢትዮጵያ እና አውሮፓ ህብረት መካከል ያለውን የኢኮኖሚ ትብብር ማጠናከርና አዳዲስ የኢንቨስትመንት እድሎችን መጠቀም በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ ነው።

የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ በፎረሙ ላይ የኢትዮጵያን የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም በዝርዝር አስረድተዋል።

ሪፎርሙ የግል ኢንቨስመንት መሳብ እና ኢትዮጵያ ከዓለም ኢኮኖሚ ጋር ያላትን ትስስር የበለጠ ማጠናከርን ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።

በፎረሙ መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉ ባለስልጣናት የኢትዮጵያ እና የአውሮፓ ህብረት የኢኮኖሚ ትብብር እያደገ መምጣቱን አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ እና የአውሮፓ ህብረት ኢንቨስትመንት ፎረም በኢትዮጵያ ተቋማትና በአውሮፓ ኩባንያዎች መካከል በኢኖቬሽን፣ በእሴት መጨመርና የጋራ ብልጽግናን መደገፍ ላይ ያላቸውን ትብብር ማጠናከር የሚያስችል ስትራቴጂካዊ ማዕቀፍ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስቴር ለኢዜአ በላከው መረጃ አመልክቷል።

ኢትዮጵያ እና የአውሮፓ ህብረት የንግድ፣ ኢንቨስትመንት እና ኢኮኖሚያዊ ትብብርን ለማጎልበት ያላቸውን የጋራ ቁርጠኝነት የሚያረጋግጥ እንደሆነም ገልጿል።

ፎረሙ የፈረንሳይ ድርጅቶች በአለም አቀፍ ደረጃ ኢንቨስትመንት ተሳትፎ እንዲኖራቸው የሚሰራ እና የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶችን በሚደግፈው ሜዴፍ ኢንተርናሽናል እና በአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ትብብር የተዘጋጀ ሲሆን በአራት የኢንቨስትመንት ዘርፎች ማለትም በአቪዬሽን፤ በታዳሽ ኃይል፤ በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ መሰረተ ልማት እና በዲጂታል ቴሌኮሙኒኬሽን ላይ ያተኮረ ነው።

የኢትዮጵያ- የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ፎረምም ይህንን እያደገ ያለ ትብብር ያሳያልም ተብሏል።

የኢትዮጵያ እና አውሮፓ ህብረት ከግማሽ ክፍለ ዘመናት በላይ ጸንቶ የቆየ ወዳጅነት ነው።

የሁለቱ ወገኖች ትብብር በአውሮፓ እና አፍሪካ ሀገራት ላለው ግንኙነት በምሳሌነት የሚጠቀስ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም