ቀጥታ፡

አዲሱ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ዓለምን የማስተሳሰር አቅም የሚጨምር ነው- የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 24/2018(ኢዜአ)፦ በቢሾፍቱ የሚገነባው አዲሱ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ዓለምን የማስተሳሰር አቅም የማጠናከር ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ አለው ሲሉ የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ ገለጹ።

የኢትዮጵያ እና የአውሮፓ ህብረት ኢንቨስትመንት ፎረም ዛሬ በፈረንሳይ ፓሪስ ተጀምሯል።

የፎረሙ አካል የሆነ እና በቢሾፍቱ በሚገነባው አዲስ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ግንባታ ላይ ያተኮረ ውይይት ተደርጓል።


 

በውይይቱ ላይ የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው፣ የአየር ማረፊያው ግንባታ አጋር የሆነው ዓለም አቀፉ አማካሪ ድርጅት ዳር አል-ሃንዳሳህ እና የግንባታው ከፍተኛ አማካሪ የሆነው ዓለም አቀፍ ተቋም ኬፒኤምጂ ተወካዮች ተገኝተዋል።

አየር ማረፊያው ከአውሮፓ ኩባንያዎች ጋር ኢንቨስትመንት እና አጋርነት የሚፈጥር ትልቅ እድል መሆኑ ተገልጿል።

የገንዘብ ሚኒስትሩ ዓለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ ሁኔታ የሚገነባው አየር ማረፊያ ለውጥ ለማምጣት፣ ብልጽግናን ለማረጋገጥ እና ዓለም አቀፍ ትስስርን ለማጠናከር ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ አለው ብለዋል።


 

የኤርባስ የአፍሪካ ኃላፊ ፌዴሪኮ ቡልቶ ኩባንያው ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ጋር ያለውን ትብብር ለማጠናከር እንደሚሻ ገልጸዋል።

የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ የኢትዮጵያ አየር መንገድ እንደ ኤምሬትስ እና ኳታር አየር መንገዶች ዓለምን የማስተሳሰር ትልቅ አቅም እንደሚፈጥርለት ተናግረዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች የአየር ማረፊያ ግንባታውን አስመልክቶ ጠቃሚ ግንዛቤ ማግኘታቸው ተገልጿል።

የአውሮፓ ባለሀብቶች በአየር ማረፊያው ግንባታ ለመሳተፍ ፍላጎት ያሳዩበት መድረክ መሆኑንም የገንዘብ ሚኒስቴር ለኢዜአ በላከው መረጃ አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም