በመካከለኛው፣ምስራቅ እና የደቡባዊ ደጋማ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ የሌሊቱና የማለዳው ቅዝቃዜ እየጨመረ ይሄዳል - ኢዜአ አማርኛ
በመካከለኛው፣ምስራቅ እና የደቡባዊ ደጋማ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ የሌሊቱና የማለዳው ቅዝቃዜ እየጨመረ ይሄዳል
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 24/2018(ኢዜአ)፦በመካከለኛው፣ምስራቅ እና የደቡባዊ ደጋማ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ የሌሊቱና የማለዳው ቅዝቃዜ ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ እንደሚሄድ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
ኢንስቲትዩቱ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው በመካከለኛው፣ምስራቅ እና የደቡባዊ ደጋማ የሀገሪቱ አካባቢዎች የአየሩ ሁኔታ እንደሚቀያየር አስታውቋል።
በደብረ ብርሃን፣አርሲ ሮቤ፣አዳባ፣ደሴ፣ባሌ ሮቤ፣አዲስ አበባ፣አደሌ፣አምባ ማሪያም፣ ኮምቦልቻ፣ አንኮበር በአብዛኛው ቀናቶች ላይ ከአምስት ዲግሪ ሴልሺየስ በታች እንደሚሆን የትንበያ መረጃዎች እንደሚያሳዩ ገልጿል።
የበጋ ወቅት ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው የሆኑት የደቡብ፣ደቡብ ምዕራብና ደቡብ ምስራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች በሚቀጥሉት አስር ቀናት ዝናብ ያገኛሉ ተብሏል።
በሌላ በኩል አብዛኛው የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ የበጋው ደረቅ፣ጸሐያማና ነፋሻማ የአየር ሁኔታ ተጠናክሮ ይቀጥላል።
በመካከለኛው፣የምስራቅ እና ደቡብ ደጋማ ቦታዎች ላይ የሌሊቱና የማለዳው ቅዝቃዜ ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ እንደሚሄድ የሚቲዎሮሎጂ መረጃዎች እንደሚያሳዩ ገልጿል።
በሚቀጥሉት አስር ቀናት ዝናብ ሰጭ የአየር ሁኔታ ክስተቶች በጋ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆኑት የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብሏል።
ደቡብ ምዕራብ፣ ደቡብ እና ደቡብ ምስራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ ይኖራቸዋል።
የመኽር ሰብል አብቃይ በሆኑት የደቡብ ምዕራብ የሀገሪቱ ክፍሎች በወሩ ያለው እርጥበት ዘግይተው ለተዘሩት፣ የእድገት ጊዜያቸውን ላልጨረሱ ሰብሎች፣ለቋሚ ተክሎችና ፍራፍሬዎች የውሃ ፍላጎት ለማሟላት ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር ገልጿል።
ያለው እርጥበት ለእንስሳት መኖም አዎንታዊ አበርክቶ እንዳለው ጠቁሟል።
በሚቀጥሉት አስር ቀናት የበጋ እርጥበት ተጠቃሚ ተፋሰሶች ላይ የተሻለ የገጸ ምድር የውሃ ፍሰት እንደሚኖራቸው የሚጠበቅ ሲሆን የተቀሩት ተፋሰሶች ዝቅተኛ እርጥበት እንደሚኖራቸው ትንበያው ያሳያል ብሏል።
አብዛኛው የባሮ አኮቦ፣ኦሞ ጊቤ፣ገናሌ ዳዋ፣ኦጋዴን፣ በመካከለኛው እና በታችኛው ስምጥ ሸለቆ፣ዋቤ ሸበሌ የተሻለ የገጸ ምድር ውሃ ፍሰት እንደሚኖራቸው ጠቁሟል።
አብዛኛው አፋር ደናክል፣አዋሽ፣ተከዜ፣መረብ ጋሽ እንዲሁም አይሻ ተፋሰሶች ላይ ደረቅ የአየር ሁኔታ ጠባይ ተጽዕኖ ስር እንደሚወድቁ የአየር ትንበያ ያሳያል ብሏል።