ተፈጥሮ ተኮር የቱሪዝም ልማት ሥራዎችን ማስፋት የሚያስችሉ ስትራቴጂዎች ተቀርጸው ተግባራዊ እየተደረጉ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ተፈጥሮ ተኮር የቱሪዝም ልማት ሥራዎችን ማስፋት የሚያስችሉ ስትራቴጂዎች ተቀርጸው ተግባራዊ እየተደረጉ ነው
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 24/2018(ኢዜአ)፦ተፈጥሮ ተኮር የቱሪዝም ልማት ሥራዎችን ማስፋት የሚያስችሉ ስትራቴጂዎች ተቀርጸው ተግባራዊ እየተደረጉ መሆኑን የቱሪዝም ሚኒስቴር አስታወቀ።
ከአስር ዓመታት በፊት የተቋቋመው የዓለም የዱር እንስሳት ፕሮግራም ዓመታዊ ጉባኤ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።
በጉባኤው ከ30 ሀገራት በላይ የተወጣጡ የዱር እንስሳት ጥበቃ ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።
የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ስለሺ ግርማ በዚህ ወቅት እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ለተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ልዩ ትኩረት በመስጠት አበረታች ውጤቶች አግኝታለች።
ቀደም ሲል በታሪክና ባህል ተኮር ቦታዎች ላይ ሰፋፊ የቱሪዝም መዳረሻ ልማት ስራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውን አንስተው፤ ይህ ተግባርም የአካባቢው ማህበረሰብ ኑሮ እንዲሻሻል፣ የስራ እድል እንዲፈጠር እና የውጭ ምንዛሬ እንዲገኝ ማስቻሉን ተናግረዋል።
በአሁን ወቅት ከቀድሞዎቹ መዳረሻዎች በተጨማሪ የተፈጥሮ ሀብትና ብሔራዊ ፓርኮችን ለቱሪዝም ልማት የማዋል ስራዎች እየተከናወኑ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡
አዲሱ የቱሪዝም ፖሊሲ ብሔራዊ ፓርኮችንና የዱር እንስሳት ልማትን ታሳቢ ያደረገ መሆኑን አንስተው፤ ይህም በኢኮ ቱሪዝም በርካታ ዜጎች ተጠቃሚ እንዲሆኑና ለተፈጥሮ ሀብትና ለዱር እንስሳት ጥበቃ ተስማሚ ከባቢ ለመፍጠር ያስችላል ብለዋል።
ኢትዮጵያ በቀጣይም ተፈጥሮ ተኮር ቱሪዝምን የበለጠ ለማስፋት በትኩረት እንደምትሰራ ተናግረዋል፡።
በተለይም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ጨምሮ የተፈጥሮ ሀብቶች ባሉባቸው ቦታዎች ላይ የቱሪዝም ልማቱን ለማስፋት ስትራቴጂዎች ተቀርጸው እየተተገበሩ መሆኑን አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሀብትና የዱር እንስሳት ጥበቃን ለማጠናከር በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ያከናወነቻቸውን ተግባራት በጉባኤው ላይ በተሞክሮ ታቀርባለች ብለዋል።
የመጥፋት አደጋ የተጋረጠባቸውን የስንቅሌ ቆርኬዎችን በሃገር በቀል ዕውቀት ቁጥራቸው እንዲጨምር ማድረግ መቻሉን እና ይህንንም ልምዷን ለሌሎች ሃገራት ለማካፈል ዝግጁ መሆኗን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን ከፍተኛ ተመራማሪ አቶ ፋኑኤል ከበደ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ በዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ለምታከናውናቸው ተግባራት ከዓለም አቀፉ የዱር ሕይወት መርሃ ግብር ድጋፍ እየተደረገላት ነው ብለዋል።
በመርሃ ግብሩ በኢትዮጵያ በአስር ጥብቅ የተፈጥሮ ቦታዎች ላይ ጥበቃ ማድረግ የሚያስችል የ12 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዶላር የሰባት ዓመታት ፕሮጀክት ይፋ መደረጉንም አንስተዋል።
በፕሮጀክቱ ጥበቃ ከሚደረግባቸው ቦታዎች፣ ባቢሌ፣ ጨበራ ጩርጩራ፣ ኦሞና ማጎ ብሄራዊ ፓርኮች እና ጉራ ፈርዳ ጥብቅ ደን ይገኙበታል።
የተፈጥሮ ሃብትና የዱር እንስሳት ጥበቃ ሥራውም ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በመሆን እየተከናወነ ነው ብለዋል።