የሀገርን ክብርና ሉአላዊነት ለማስከበር የሚያስችል የተሟላ ዝግጁነት እና አቅም ያለው ሰራዊት ተገንብቷል- ሜጀር ጀነራል አዳምነህ መንግስቴ - ኢዜአ አማርኛ
የሀገርን ክብርና ሉአላዊነት ለማስከበር የሚያስችል የተሟላ ዝግጁነት እና አቅም ያለው ሰራዊት ተገንብቷል- ሜጀር ጀነራል አዳምነህ መንግስቴ
ጅማ፤ ጥቅምት 24/2018(ኢዜአ)፦ የሀገርን ክብርና ሉአላዊነት ለማስከበር የሚያስችል የተሟላ ዝግጁነት እና አቅም ያለው ሰራዊት መገንባቱን የሀገር የመከላከያ ሰራዊት የሰላም ማስከበር ማእከል ኃላፊ ሜጀር ጀነራል አዳምነህ መንግስቴ ገለጹ።
የዳሎል ማዕከላዊ እዝ አባላት እና የሀገር መከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ መኮንኖች "እንዳይደገም መቼም አንረሳውም" በሚል መሪ ሃሳብ የጥቅምት 24ቱን ጥቃት በተለያዩ ዝግጅቶች አስበውታል።
በዚሁ ሁነት ላይ የተገኙት በሀገር መከላከያ ሰራዊት የሰላም ማስከበር ማእከል ሃላፊ ሜጀር ጀነራል አዳምነህ መንግስቴ፤ መከላከያ ሰራዊት የሀገርን ክብርና ሉአላዊነት ለማስከበር የሚያስችል ዝግጁነትና የተሟላ አቅም የገነባ መሆኑን ገልጸዋል።
የሰራዊቱ ወትሮ ዝግጁነትና የግዳጅ አፈፃፀም ብቃት ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው ከሀገርም ባለፈ ለሌሎች ሃገራት የጀግንነት መገለጫ እና የሰላም ተምሳሌት የሆነ ብቁ ሰራዊት ተገንብቷል ብለዋል።
የሀገርን ክብርና ሉአላዊነት ለማስከበር የሚያስችል የተሟላ ዝግጁነትና ጠንካራ አቅም ያዳበረ ሰራዊት መገንባቱን አንስተው ለማንኛውም ግዳጅ ሰራዊቱ ዝግጁ መሆኑንም አረጋግጠዋል።
የዳሎል ማእከላዊ እዝ አባላትም በተሰማሩበት የግዳጅ ቀጣና ሁሉ በጀግንነት ውጤታማ ተልእኮዎችን በመፈፀም የሚታወቁ መሆኑን አንስተው ይህንኑ አጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል።
የዳሎል ማእከላዊ እዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጀነራል ዘውዱ በላይ በበኩላቸው ጥቅምት 24ን ማስታወስ ያስፈለገው ሰራዊቱ ለሀገር የከፈለውን መስዋእትነት ለማሳየትና መሰል ጥፋቶች በቀጣይ እንዳይደገሙ ትውልዱ እንዲማርበት በማሰብ ነው ብለዋል።
የሀገር መከላከያ ሰራዊት ለሀገር አንድነት እና ሰላም መረጋገጥ በጽናትና በጀግንነት መቆሙን ገልጸው ለቀጣይም የላቀ ዝግጁነት ያለው መሆኑን አረጋግጠዋል።
በዚሁ መድረክ ላይ የውይይት መነሻ ጽሑፍ ያቀረቡት በጅማ ዩኒቨርስቲ የታሪክ መምህር ንጉሱ አደም (ዶ/ር)፤ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በጀግንነት ጸንቶ የቆመ፣ የሀገር ህልውና መሰረት ብሎም የዓለም የሰላም ማስከበር ተምሳሌት መሆኑን አንስተዋል።
የሀገሩን ዳር ድንበር ከማስከበር አልፎ በተለያዩ ሃገራት በሰላም ማስከበር ተልእኮ የተመሰከረለት ጠንካራ ሰራዊት መሆኑን አስታውሰው በዚህም ክብርና አድናቆት ሊቸረው ይገባል ብለዋል።
በጅማ ከተማ በተካሄደው መርሀ ግብር ላይ የሰራዊቱ አባላትና ከፍተኛ መኮንኖች፣ የመንግስት የስራ ሀላፊዎች፣ ምሁራን፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሀይማኖት አባቶችና የተለያዩ የማህበረሰብ ተወካዮች ተገኝተዋል።