በአዲስ አበባ በ2018 ዓ.ም የበጋ በጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ911 ሺህ በላይ ነዋሪዎች ተጠቃሚ ይሆናሉ-ኮሚሽኑ - ኢዜአ አማርኛ
በአዲስ አበባ በ2018 ዓ.ም የበጋ በጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ911 ሺህ በላይ ነዋሪዎች ተጠቃሚ ይሆናሉ-ኮሚሽኑ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 24/2018(ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ በ2018 ዓ.ም የበጋ በጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ911 ሺህ በላይ ነዋሪዎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኅብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን ገለጸ፡፡
ኮሚሽኑ በበጋ ወራት የሚከናወነውን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት "በጎ ፈቃደኝነት፤ ለማኅበረሰብ ለውጥ" በሚል መሪ ሃሳብ በይፋ አስጀምሯል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አማካሪ አቶ ጥላሁን ሮባ፤ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በነዋሪዎች ሕይወትና በከተማዋ እያመጣ ያለውን ውጤት ማስቀጠል ይገባናል ብለዋል፡፡
ባለፉት ጊዜያት በርካቶች ከበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቁመው ይህን ለማስቀጠልም በጎ ፈቃደኞች በጎ ተግባራቸውን ሊያስቀጥሉ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ የኅብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አስራት ንጉሴ፤ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት በርካታ ዜጎች በማኅበራዊና ኢኮኖሚ ተጠቃሚ መሆን መቻላቸውን ገልጸዋል፡፡
ባለፉት ዓመታት ለዘርፉ በተሰጠው ልዩ ትኩረት በአዲስ አበባ ከተማ 42 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር የሚገመቱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች መከናወናቸውን ተናግረዋል፡፡
ለአብነትም የቤት ግንባታና እድሳት፣ ደም ልገሳ እና አረንጓዴ አሻራን ጠቅሰዋል፡፡
የኮሚሽኑ የበጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ዳይሬክተር ዳዊት ሙሉጌታ በበኩላቸው፤ በዘንድሮው የበጋ ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት 9 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ግምት ያለው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ይከናወናል ብለዋል፡፡
ከ911 ሺህ በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ጠቅሰው የቤት ግንባታና እድሳት፣ ማዕድ ማጋራት፣ የጤና አገልግሎት እና የአረንጓዴ ልማት ከሚከናወኑ ሥራዎች መካከል ናቸው ብለዋል፡፡
አረጋውያንና አቅመ ደካሞችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ 1ሺህ 900 ቤቶች እንደሚገነቡም አብራርተዋል።
በመርኃ ግብሩ ላይ የተገኙት በጎ ፈቃደኞች በተከታታይ ዓመታት በመዲናዋ በሚከናወኑ የበጎ ፈቃድ ተግባራት በንቃት ሲሳተፉ መቆየታቸውን ገልጸዋል።
በጎ ፈቃደኞች ማሬ ሙሉጌታ እና ጌታሁን ብርሃኑ ለበጋው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
በሚከናወነው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በድግግሞሽ ከ500 ሺህ በላይ በጎ ፈቃደኞች ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ በመርኃ ግብሩ ተጠቁሟል።