ቀጥታ፡

የካንሰር ሕክምና በቅርበት ማግኘታችን ከእንግልትና ካልተገባ ወጪ ታድጎናል - ታካሚዎች

ሀዋሳ ፤ ጥቅምት 24/2018(ኢዜአ)፦የካንሰር ሕክምና በቅርበት ማግኘታቸው ከእንግልትና ካልተገባ ወጪ እንደታደጋቸው በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የካንሰር ሕክምና ማዕከል ታካሚዎች ገለጹ።

መንግስት የሕክምና አገልግሎትን ለዜጎች ተደራሽ ከማድረግ አንጻር የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።

በተለይ በሀገር ውስጥ እንደ ካንሰር ያሉ የጤና ችግሮችን ዜጎች በአቅራቢያቸው መታከም እንዲችሉ የተለያዩ ሥራዎች በመከናወን ላይ ናቸው። 

ባለፉት አምስት ዓመታት የካንሰር ሕክምናን በክልሎች ተደራሽ የማድረግ ሥራ በመሰራቱ በአሁኑ ወቅት በማስተማሪያ ሆስፒታሎች  ጭምር ሕክምናውን የመስጠት ሥራ ተጀምሯል።


 

ይህም ሕክምናውን ለማግኘት በአዲስ አበባ ጥቁር አንበሳ እና ጳውሎስ ሆስፒታሎች የነበረውን ወረፋና የሰዎች መጨናነቅ እያቃለለ መሆኑ ነው የተመላከተው። 

የካንሰር ሕክምና ከተጀመረባቸው መካከል የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የካንሰር ሕክምና ማዕከል አንዱ ሲሆን ታካሚዎችም ሕክምናውን በቅርበት ማግኘታቸው ቀደም ሲል ሲደርስባቸው የነበረውን እንግልትና ወጪ እንዳስቀረላቸው ተናግረዋል። 

ከሆስፒታሉ ታካሚዎች መካከል ከአርባ ምንጭ በሪፈር ተልከው እንደመጡ የተናገሩት አቶ ችለነው መሰለ፣ በማዕከሉ በተደረገላቸው ምርመራ ችግሩ የደም ካንሰር መሆኑ እንደታወቀላቸው ገልጸዋል።

ለካንሰር ሕክምና ወደ አዲስ አበባ ከተማ መምጣት ሳያስፈልግ አገልግሎቱን በቅርበት ማግኘታቸው ከወጪና ከእንግልት ታድጎኛል ሲሉም ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት በሆስፒታሉ ተገቢ የሕክምና አገልግሎት እያገኙ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በአንጀት ካንሰር የታመሙ እናቱን ለማሳከም ከምዕራብ አርሲ ዞን ኮኮሳ ወረዳ እንደመጣ የተናገረው ወጣት ጀማል መሀመድ በበኩሉ በአዲስ አበባ፣ ሻሸመኔ፣ ጎባና ሌሎች ሆስፒታሎች እናቱን ለማሳከም ብዙ መድከሙን ገልጿል። 


 

ወደካንሰር ማዕከሉ ከመጡ አንደ ሳምንት እንደሆናቸውና በአሁኑ ወቅት ሕክምናቸውን በጥሩ ሁኔታ እየተከታተሉ መሆናቸውን ገልጿል።

የካንሰር ሕክምና ማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር ሰለሞን ሁነኛው እንዳሉት ማዕከሉ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ ሁለት ዓመት ሆኖታል።


 

እስካሁንም ከ5 ሺህ በላይ ለሚሆኑ አዋቂና ሕጻናት የካንሰር ሕክምና አገልግሎት መሰጠቱን ጠቁመዋል።


 

ማዕከሉ ከሲዳማ፣ ከደቡብ ኢትዮጵያ እና ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች እንዲሁም ከኦሮሚያ ባሌ፣ ቦረናና ጉጂ ዞኖች የሚመጡ ሕሙማንን እያገለገለ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

በማዕከሉ የህጻናትና የደም ካንሰር ሰብ ስፔሻሊስት ሙሉአለም ንጉሴ (ዶ/ር) በበኩላቸው እንዳሉት የካንሰር ማዕከሉ የህጻናትን ህክምና ክፍል በማቋቋም በሽታ የመለየትና የማከም ሥራ እየሰራ ይገኛል።


 

በቀን እስከ ዘጠኝ ሕጻናት የሕክምና አገልግሎት እንደሚያገኙ ጠቁመው፣ በሕጻናት ላይ በአብዛኛው የደም ካንሰር፣ የጭንቅላት እጢ፣ የአጥንት፣ የኩላሊትና ሌሎች የካንሰር ሕመሞች ይስተዋላሉ ብለዋል።

በካንሰር የተያዙ ሕጻናትን በፍጥነት ወደ ሕክምና ማምጣት ከተቻለና ተገቢ ሕክምና ካገኙ የመዳን ዕድል እንደሚኖራቸው አመልክተዋል።

በማዕከሉ ለካንሰር ሕመም የጨረር ሕክምና መስጫ መሳሪያ አንድ ብቻ መሆኑና ለ24 ሰዓት ያለሟቋረጥ አገልግሎት እንዲሰጥ በመደረጉ ጫናው ከፍተኛ መሆኑም ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም