ቀጥታ፡

የአካባቢውን ሰላም በዘላቂነት በመጠበቅ የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ተዘጋጅተናል- ሰልጣኝ የሕግ አስከባሪዎች 

ገንዳ ውኃ፤ ጥቅምት 24/2018 (ኢዜአ):-የአካባቢውን ሰላም  በዘላቂነት በመጠበቅ  የሕግ  የበላይነትን ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት መዘጋጀታቸውን በምዕራብ ጎንደር ዞን የተመደቡ አዲስ የአድማ መከላከልና መደበኛ ፖሊስ አባላት ገለጹ።  

ሰልጣኝ የሕግ አስከባሪዎቹ ወደ  ዞኑ ሲገቡ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።  

ከሰልጣኞቹ መካከልም የአድማ መከላከል ፖሊስ ሙሐመድ ሱሌማን በሰጠው አስተያየት፤ ሀገርንና ሕዝብን ለማገልገል በነበረው ፍላጎት  ወደ ፖሊስ ተቋም በመቀላቀል ተገቢውን ፖሊሳዊ ስልጠና መውሰዱን ተናግሯል። 


 

በስልጠና ቆይታው ያገኘውን እውቀትና ፖሊሳዊ ጥበብ በመጠቀም የአካባቢውን ሰላም በዘላቂነት በመጠበቅ የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የድርሻውን ለመወጣት ቁርጠኛ መሆኑን ገልጿል። 

ኮንስታብል ዳዊት ሞላ በበኩሉ፤ የተሰጠውን ሀገራዊና ሕዝባዊ አደራ ለመወጣት አበክሮ እንደሚሰራ ገልፆ የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ሁሉ የበኩሉን ሚና በመወጣት ለዘላቂ ሰላም ግንባታ እንደሚተጋ ተናግሯል። 


 

ሰልጣኞቹ የተጣለባቸውን ሕዝባዊ አደራ ታማኝነትን በጠበቀ አግባብ ለመወጣት መዘጋጀታቸውንም አረጋግጠዋል።

የምዕራብ ጎንደር ዞን  አስተዳዳሪ ተወካይና የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኃላፊ አቶ መሰንበት መልካሙ እንደገለጹት፤ ሰልጣኝ የሕግ አስከባሪዎች ሰላምን ለማፅናት በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ተገቢው ድጋፍና ክትትል ይደረጋል። 


 

የዞኑ ሕዝብ ሰላም ወዳድና የልማት አርበኛ መሆኑን ጠቅሰው፤ ሕብረተሰቡ ለፀጥታ አካሉ ተልዕኮ ስኬታማነት እያደረገ ያለውን ትብብር አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አሳስበዋል።

መከላከያ ሰራዊት የ504ኛ ኮር ምክትል አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል ቾምቤ ወርቁ በበኩላቸው፤ ሰራዊቱና የክልሉ የፀጥታ ኃይል   የጥፋት ኃይሎችን ተልዕኮ በቅንጅት በማምከን አኩሪ ገድል እየፈፀሙ እንደሚገኙ ገልጸዋል። 


 

ሰላምን የማፅናትና የሕግ የበላይነትን የማረጋገጥ ተግባር እንደ ሁልጊዜው ሁሉ በቀጣይም በሕዝቡ የተቀናጀ ተሳትፎ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም