የባንዳ ስራ ላይ የተሰማሩ ኃይሎች ከሀገር ክህደት ተግባራቸው ሊቆጠቡ ይገባል - ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ - ኢዜአ አማርኛ
የባንዳ ስራ ላይ የተሰማሩ ኃይሎች ከሀገር ክህደት ተግባራቸው ሊቆጠቡ ይገባል - ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 24/2018(ኢዜአ)፦ የባንዳ ስራ ላይ የተሰማሩ ኃይሎች ከሀገር ክህደት ተግባራቸው ሊቆጠቡ እንደሚገባ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ ገለጹ።
የመከላከያ ሰራዊት የሰሜን ዕዝ ጥቃት የሚዘከረው የተፈጸመው አሳዛኝ ድርጊት መቼም እንዳይደገም ለማስታወስ መሆኑንም የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ ገልጸዋል።
የመከላለከያ ሰራዊት የሰሜን ዕዝ የተፈጸመበት ጥቃት አምስተኛ ዓመት ዝክረ ሰሜን ዕዝ "እንዳይደገም መቼም አንረሳውም" በሚል መሪ ሀሳብ በቢሾፍቱ የኮማንዶና አየር ወለድ ዕዝ ማሰልጠኛ ማዕከል ተከብሯል።
ከአምስት ዓመት በፊት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም የጀግናው መከላከያ ሰራዊት አካል የሰሜን ዕዝ ክህደት እንደተፈፀመበት ይታወቃል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ፣ የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል አበባው ታደሰና ሌሎች ከፍተኛ ጄኔራል መኮንኖችና የመከላከያ ሰራዊት አባላት ተገኝተዋል።
የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ጥቅምት 24 ቀን የሰሜን ዕዝ ዝክረ ሰማዕታት ቀን ነው።
የመከላከያ ሰራዊት የሀገሩን ዳር ዳር ድንበር በማስከበር የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ ዝግጁ መሆኑንም አውስተዋል።
የሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ለትግራይ ክልል ምሽግና አጥር እንደነበር ገልጸው፤ እስከ አሁን ከሰሜን ዕዝ ውጪ በራሱ ዜጎች ጥቃት የደረሰበት አጋጣሚ እንዳልተፈጠረ ተናግረዋል።
የመከላከያ ሰራዊት ከራሱ ቀንሶ በትግራይ ብዙ ትምህርት ቤት፣ ጤና ተቋማትና የግብርና ልማት እንዳከናወነ ገልጸው፣ ጥቅምት 24 ቀን የተፈጸመው ድርጊት ግን በኢትዮጵያ ታሪክ ጥቁር ነጥብ ነው ብለዋል።
የሰሜን ዕዝ ጥቃት መቼም እንደማይረሳ ገልጸው፤ ቀኑ የሚዘከረው መቼም እንዳይደገም መሆኑን አንስተዋል።
ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ዕለቱን ሲያስታውሱ፤ መንግሥት በወቅቱ በተለያዩ አካባቢዎች የተለኮሱ ግጭቶችን ለማብረድ የሚታትርበት እንጂ የጦርነት ዝግጁነት እንዳልነበረው አውስተዋል።
መንግሥት ሁልጊዜም ለሰላማዊ መንገድ በሩን ክፍት ማድረጉን ጠቁመው፤ ከትላንት ባለመማር የሚደረግ ፉከራ መቆም አለበት ብለዋል።
የቀድሞው ህወሓት ጥቂት አባላት የታጠቁ ኃይሎችን በመደገፍ፣ ሀገር ለማፍረስ ከጎረቤት ሀገር ጋር ግንኙነት በመፍጠር፣ በዲ.ዲ.አር የተሰባሰቡትን በመበተን የፕሪቶሪያን የሰላም ስምምነት እየጣሱ መሆኑንም ገልጸዋል።
የባንዳ ስራ ላይ የተሰማሩ እነዚህ ህዝቡን የማይወክሉ ኃይሎች ከሀገር ክህደት ተግባራቸው ሊቆጠቡ እንደሚገባም ተናግረዋል።
የመከላከያ ሰራዊት ሥነ ልቦና ግንባታ ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጄኔራል እንዳልካቸው ወልደኪዳን በበኩላቸው፤ ከአምስት ዓመት በፊት በሰሜን ዕዝ የሰራዊት አባላት ላይ የተፈፀመው ጥቃት በሀገር ሉዓላዊነት ላይ የተቃጣ ደባ መሆኑን ጠቁመዋል።
ዝክረ ሰሜን ዕዝ ወቅቱን በሚመጥን መልኩ እየተከበረ ነው ብለዋል።
የተፈጸመው ጥቃት እንዳይደገም መቼም አንረሳውም ያሉት ሜጀር ጄኔራል እንዳልካቸው፣ ጥቃቱን ለመመከት ሲሉ መስዋዕትነት የከፈሉ የሰራዊቱ አባላትን ለማስታወስ እና ለተጋድሏቸው ዕውቅና ለመስጠት እንደሚዘከር ገልጸዋል።