ቀጥታ፡

ከምክር ቤቱ የመጨረሻ ዓመት የሥራ ዘመን ምን ይጠበቃል?

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 24/2018(ኢዜአ)፦ ከ6ኛው ዙር ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመጨረሻ ዓመት የሥራ ዘመን የሚጠበቁ ጉዳዮች ምንድ ናቸው?

6ኛው ዙር የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አምስተኛ ዓመት የሥራ ዘመን ዘንድሮ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።

ምክር ቤቱ በሕገ-መንግስቱ በተሰጠው ሥልጣንና ተግባር መሰረት ሕግ ያወጣል፣አስፈጻሚ ተቋማትን ይከታተላል፣ ይቆጣጠራል።

የፓርላማ ዲፕሎማሲ እንዲሁም የህዝብ ውክልና ሥራዎችን ያከናውናል።

ምክር ቤቱ ባለፉት አራት ዓመታት ሀገራዊ ለውጡን የበለጠ የሚያሳልጡና የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች የሚመልሱ ተግባራትን ሲያከናውን መቆየቱን የምክር ቤቱ አባላት ያነሳሉ።

በጉዳዩ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የምክር ቤቱ አባላት በቀሪ የሥራ ጊዜያቸው የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ዕድገት ለማረጋገጥ የተጀመሩ ሥራዎች የበለጠ ውጤታማ እንዲሆኑ በትጋት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

ከምክር ቤቱ አባላት መካከል መብራቱ ዓለሙ (ዶ/ር) በተያዘው ዓመት ከሚጠበቁ ጉዳዮች መካከል ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ በተመረጡ አጀንዳዎች ላይ የሚያደርገው ውይይት ነው ብለዋል።


 

ኮሚሽኑ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ሥብራት ለመጠገንና ነባር ችግሮችን በምክክር የመፍታት ባህል ለማዳበር መፍትሄ እንደሚያመጣ እንደታመነበትም ነው ያነሱት።

ምክር ቤቱ በቀሪ የሥራ ዘመኑ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ በፍጥነት ወደ ሥራ እንዲገባና ችግሮች በምክክር መፍትሄ እንዲያገኙ አበክሮ ይሰራል ብለዋል።

የፓርላማ ወዳጅነት ቡድኖች ኢትዮጵያ  ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያላትን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር በትኩረት እንደሚሰሩ የገለጹት ደግሞ ሌላው የምክር ቤት አባል ሳዲቅ አደም ናቸው።


 

በፓርላማ ዲፕሎማሲ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅሞች የሚያስከብሩና የሀገሪቷን የልማት ፍላጎትን የሚያስረዱ ጉዳዮች ላይ በስፋት ይሰራል ብለዋል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል አለሙ ጎንፋ (ዶ/ር) በበኩላቸው በተያዘው በጀት ዓመት በኢትዮጵያ በርካታ የልማት ፕሮጀክቶች መጀመራቸውን አስታውሰዋል።


 

የምክር ቤቱ አባላትም በመጨረሻ ዓመት የሥራ ጊዜያቸው እነዚህ ፕሮጀክቶች በተሻለ ፍጥነትና ፈጠራ እውን እንዲሆኑ የተለየ ድጋፍና ክትትል ያደርጋሉ ብለዋል።

ለሚቀጥለው ምክር ቤት አስቻይ ሁኔታዎችን ማመቻቸት የ5ኛ ዓመት የምክር ቤት አባላት ድርሻ መሆኑንም አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም