በዲጂታል መልክ የሚሰጥ የዕፅዋት ንፅህና ማረጋገጫ ወረቀት (ኢ-ፋይቶ) ሥርዓት ተግባራዊ መደረግ የኢትዮጵያ ግብርና ምርቶች ላይ ተወዳዳሪነትን ያሳድጋል - ኢዜአ አማርኛ
በዲጂታል መልክ የሚሰጥ የዕፅዋት ንፅህና ማረጋገጫ ወረቀት (ኢ-ፋይቶ) ሥርዓት ተግባራዊ መደረግ የኢትዮጵያ ግብርና ምርቶች ላይ ተወዳዳሪነትን ያሳድጋል
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 24/2018(ኢዜአ)፦ በዲጂታል መልክ የሚሰጥ የዕፅዋት ንፅህና ማረጋገጫ ወረቀት (ኢ-ፋይቶ) ሥርዓት ተግባራዊ መደረግ የኢትዮጵያ ግብርና ምርቶች የወጭ ንግድን በማቀላጠፍ ተወዳዳሪነትን በእጅጉ የሚያሳድግ መሆኑን የዘርፉ ተዋንያን ገለጹ፡፡
ኢ-ፋይቶ 'Electronic Phytosanitary Certificate' የዕፅዋት ንፅህና ማረጋገጫ ወረቀትን በኤሌክትሮኒክ መልክ የሚሰጥ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የዕፅዋት ምርቶችን ንግድ የሚያፋጥን እና ደኅንነቱ የተጠበቀ የሚያደርግ ዲጂታል መፍትሔ ነው።
የኢ-ፋይቶ ሥርዓት ለኢትዮጵያ የወጪ እና ገቢ ንግድ ከሚያስገኛቸው ቁልፍ ጥቅሞች መካከል የንግድ ቅልጥፍና፣ የኤክስፖርት ተወዳዳሪነት፣ የወጪ ቅነሳ፣ ግልጽነትና ተዓማኒነት እንዲሁም የባዮ-ደኅንነት ቁጥጥር ዋናዎቹ ናቸው።
የኢትዮጵያ ግብርና ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወንዳለ ሀብታሙ (ዶ/ር) በሰጡት አስተያየት፤ ኢ-ፋይቶ በኢትዮጵያ የግብርና ኤክስፖርት ዘርፍ በተለይም በሆርቲካልቸር ኢንዱስትሪ ላይ ከፍተኛ ለውጥ ያመጣል።
ሥርዓቱ ከ188 ሀገራት፣ ከተባበሩት መንግሥታት፣ ከአውሮፓ ህብረት፣ ከአፍሪካ ህብረት እና ከኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን ጋር መገናኘቱን ጠቁመው፤ ይህም የኢትዮጵያ ምርቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸው ተዓማኒነት እንዲጨምር እንደሚያስችል ገልጸዋል።
የሥርዓቱ ተግባራዊ መሆን ባለሥልጣኑ የዓለም አቀፍ እፅዋት ጥበቃ ስምምነት መስፈርቶችን ለማሟላቱ ማሳያ መሆኑን ጠቁመው፤ ለምርቶች ዓለም አቀፍ ተዓማኒነትን የሚሰጥና ተወዳዳሪነትን የሚያሳድግ ትልቅ እርምጃ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ አበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ አምራች ላኪዎች ማኅበር ዋና ዳይሬክተር ቴዎድሮስ ዘውዴ በበኩላቸው፤ በኢ-ፋይቶ ሥርዓት የግብርና ምርት ኤክስፖርት የሚያደርጉ አካላት ሁሉ የሚካተቱበት መሆኑን ተናግረዋል።
ሥርዓቱ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ምርቶችን ጥራት ለመቆጣጠር የሚያስችል እና ከሌሎች ሀገራዊ ፕሮግራሞች ጋር የተቀናጀ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በተለይም በሆርቲካልቸር የወጪ ንግድ ዘርፍ ለተሰማሩ ላኪዎች ተወዳዳሪ ሆነው እንዲቀጥሉ የሚያስችል ወሳኝ ምዕራፍ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በአበባ ምርት ላኪነት የተሰማሩት የቲናው ቢዝነስ ሼር ካምፓኒ ኦፕሬሽናል ማኔጀር ሞሲሳ ተፈሪ በበኩላቸው፤ ኢ-ፋይቶ ድርጅታቸውን ጨምሮ በሆርቲካልቸር ዘርፍ ለተሰማሩ ሁሉ እንግልትን የሚያስቀርና ተዓማኒነትን የሚጨምር ነው ብለዋል።
የምስክር ወረቀቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ በዲጂታል መንገድ ስለሚተላለፍ የምርት መዘግየትን የሚያስቀር አስተማማኝ ሥርዓት ነው ብለዋል።
ይህም የወጪ ንግድ ሂደቱን በእጅጉ የሚያቀል መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የኢ-ፋይቶ ሥርዓት መጀመር ለኢትዮጵያ የግብርና ምርቶች ላኪዎች በአፈጻጸም፣ በጊዜና በወጪ ቁጠባ ትልቅ ለውጥ የሚያመጣ ትልቅ ምዕራፍ ነው።