በዞኑ የወባ በሽታ ስርጭትን ለመቆጣጠር ህዝቡን በማሳተፍ የመከላከል ተግባር እየተከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ የወባ በሽታ ስርጭትን ለመቆጣጠር ህዝቡን በማሳተፍ የመከላከል ተግባር እየተከናወነ ነው
አዶላ፤ ጥቅምት 24/2018 (ኢዜአ) ፡-በጉጂ ዞኑ የወባ በሽታ ስርጭትን ለመቆጣጠር በህዝቡ ተሳትፎ ለወባ ትንኝ መራቢያ ምቹ የሆኑ ውሀ ያቆሩ ቦታዎችን የማዳፈን ፣የኬሚካል ርጭትና የአጎበር ስርጭት እየተካሄደ መሆኑን የጉጂ ዞን ጤና ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ተስፋዬ በሪሶ ገለፁ፡፡
ስራውን ውጤታማ ለማድረግ በበሽታው መከላከያ ዘዴዎችና ምልክት ላይ በማተኮር ለ14 ሺህ 959 ሰዎች ግንዛቤ መሰጠቱን ጠቁመዋል፡፡
በዚህም 19 ሺህ 250 ካሬ ሜትር ለወባ መራቢያ አመቺ የሆኑ ውሀ ያቆሮ ቦታዎችን ማዳፈን ፣34 ሺህ 990 ካሬ ሜትር የሚሸፍን የወባ መራቢያ ቦታ ላይ የኬሚካል ርጭት መደረጉን ገልጸዋል፡፡
በዞኑ የጤና ጥበቃ ስራን ውጤታማ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ህዝቡና የባለድርሻ ተሳትፎ እንዲጠናከር ጠይቀዋል፡፡
በዞኑ ሰባ ቦሩ ወረዳ የቀንጢቻ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ኢያሱ ጠዴቻ፣ የክረምቱ መውጣትን ተከትሎ የሚከሰት የወባ በሽታን ለመከላከል በጤና ባለሞያዎች የተሰጣቸውን ግንዛቤ እየተገበሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከአከባቢያቸው ነዋሪዎች ጋር በመተባበር ለወባ ትንኝ መራቢያ ምቹ የሆኑ ውሀ ያቆሩ ስፍራዎችን ማጽዳታቸውን ገልፀዋል።
የዚሁ ወረዳና ቀበሌ ነዋሪ አቶ መልካሙ ነጋሳ የወባ በሽታን ለመከላከል በጤና ባለሙያዎችና በበጎ ፈቃደኞች ያገኙትን ግንዛቤ በመጠቀም የወባ መራቢያ ቦታዎችን ማጽዳታቸውን ተናግረዋል፡፡
በጋራ አካባቢያቸውን የማጽዳትና አጎበርን በአግባቡ መጠቀም እንዲሁም በመንግስት የተደረገው የመድሀኒት ርጭት የወባ በሽታ ስጋታቸውን መቀነሱን ጠቁመዋል፡፡