በክልሉ መደጋገፍን መሠረት ያደረጉ ማህበራዊ ትስስሮች ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ መደጋገፍን መሠረት ያደረጉ ማህበራዊ ትስስሮች ተጠናክረው ይቀጥላሉ
ሰመራ፣ጥቅምት 24፣2018(ኢዜአ):- በአፋር ክልል መደጋገፍን መሠረት ያደረጉ ማህበራዊ ትስስሮችን የማጠናከሩ ተግባር በትኩረት እንደሚከናወን የአፋር ክልል ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ገለጸ።
ቢሮው በገጠር ልማታዊ ሴፍቲኔት መርሃ ግብር የቀጥታ ድጋፍ ተጠቃሚዎች የተሻለና የተጠናከረ ድጋፍ የሚያገኙበት ሁኔታ ለማሳደግ የሚያስችል ለሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ፅህፈት ቤት ኃላፊዎች፣ ለማህበራዊ ደህንነት ባለሙያዎችና ለማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አስተባባሪዎች ስልጠና መስጠት ጀምሯል።
በዕለቱ ተገኝተው መድረኩን የከፈቱት የክልሉ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ነስሮ ኡዳ እንዳሉት በክልሉ መደጋገፍን መሠረት ያደረጉ ማህበራዊ ትስስሮችን የማጠናከሩ ተግባር በትኩረት ይከናወናል።
በሴፍቲኔት መርሃ ግብር እየተደረገ ያለው ድጋፍ በቂ አለመሆኑን አንስተው፤ ማህበራዊ ትሰስርን በማጠናከርና በማስተባበር የተለያዩ ባለድርሻዎችን በማሳተፍ የሚደረግላቸው እገዛ ሊጠናከር ይገባል ብለዋል።
በየወረዳዎቹ የሚገኙና ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው የህብረተሰብ ክፍሎችን የጤና መድህን ወጪያቸውን በመሸፈንና አስፈላጊነት ያለውን እገዛ የማድረጉ ተግባርም በስፋት ይሰራል ብለዋል ።
በዚህ ረገድ የወረዳ ፅህፈት ቤት ኃላፊዎችና ባለሙያዎች የተዋቀሩትን ኮሚቴዎች በማጠናከር የሚደረገው ድጋፍ እንዲጨምር ሚናቸውን መወጣት እንደሚገባቸውም አስገንዝበዋል።
ከፈንቲ ራሱ ዞን አውራ ወረዳ በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ፅህፈት ቤት የማህበራዊ ጉዳይ ዳይሬክተር አቶ ሙጃሂድ መሐመድ እንዳለው በወረዳው ለሚገኙና ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው አቅመ ደካማ ወገኖች በሴፍቲኔት የታገዘ ድጋፍ ተደርጓል።
ይህንን ማህበራዊ ኃላፊነት በመወጣት ረገድ ህብረተሰባችንን በማስተባባበር ቀጣይነት ያላቸው ስራዎችን ማከናወን ላይ ትኩረት ይደረጋል ብለዋል።
የመደጋገፍ ተግባሩ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን እፎይታን የሰጠ መሆኑን የገለፀው ደግሞ ከአፋምቦ ወረዳ የመጣው በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ፅህፈት ቤት የማህበራዊ ጉዳይ ዳይሬክተር አቶ ኢሴ መሐመድ ናቸው።
የተባባበረ ድጋፍን ማጠናከር ላይ ያተኮረው ስልጠናም ለሁለት ቀናት እንደሚቆይም ታውቋል።