ቀጥታ፡

በሀላባ ዞን የደረሰ ሰብል ከብክነት በጸዳ መንገድ በኮምባይነር እየተሰበሰበ ነው

ሀላባ ፤ ጥቅምት 24/2018(ኢዜአ)፦ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሀላባ ዞን የደረሰ ሰብል ከብክነት በጸዳ መንገድ በኮምባይነር እየተሰበሰበ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ ገለፀ፡፡

በመኸር ወቅት ለምቶ እየተሰበሰበ ያለውን ምርት አስመልክተው ለኢዜአ ማብራሪያ የሰጡት የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ምክትል ሃላፊ አቶ አብድራህማን ኡስማን በዞኑ በ2017/18 የመኸር ወቅት ከ29 ሺህ 800 ሄክታር በላይ መሬት ለምቷል።


 

ከዚህም ከ1 ሚሊዮን 500 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፣ የሰብል ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግም ለክላስተር ልማት፣ ለቴክኖሎጂና ለግብአት አቅርቦት ትኩረት መሰጠቱን ተናግረዋል።

በስንዴና በቆሎ ከለማው መሬት ቀድመው የደረሰው ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ እንዳይበላሽ ከብክነት በጸዳ መልኩ በኮምባይነር በመታገዝ እየተሰበሰበ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በዚህም የአካባቢው አርሶ አደሮች ጭምር የደረሰ የስንዴ ሰብላቸውን በኮምባይነር ታግዘው እየሰበሰቡ ይገኛሉ ብለዋል።


 

በሀላባ ዞን የዌራ ዲጆ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዲ አደም በበኩላቸው በወረዳው የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ግብአት በወቅቱ ከማቅረብ ባለፈ የግብርና ባለሞያዎች ለአርሶ አደሩን በቅርበት እየደገፉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅትም የደረሱ ሰብሎቹ ከብክነት በጸዳ መልኩ የመሰብሰብ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመው፣ በክረምቱ የመኸር አርሻ ለስንዴና ለበቆሎ ምርጥ ዘር ብዜት ስራም ትኩረት መሰጠቱን አመልክተዋል።

በዞኑ በዌራ ዲጆ ወረዳ የሚገኘው የአለማየሁ መኮንን እርሻ ልማት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ስዩም ኃይለጊዮርጊስ እንደገለጹት እርሻ ልማቱ በ560 ሄክታር መሬት ላይ የስንዴ ምርጥ ዘር በዘመናዊ መንገድ አልምቷል።


 

በአሁኑ ወቅት ሰብሉ ለአጨዳ በመድረሱ በኮምባይነር መሰብሰብ መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡

ከእርሻ ዝግጅት ሥራ እስከ ምርት አሰባሰብ ድረስ ያለውን ሂደት በሜካናይዜሽን መደገፉ ምርታማነትን ለማሳደግ፣ ጊዜን ለመቆጠብና ግብአት በአግባቡ ለመጠቀም ፋይዳው የጎላ መሆኑንም አመልክተዋል።

በ77 ሄክታር መሬት ላይ በክላስተር ያለሙትን የስንዴ ሰብል ከብክነት በጸዳ መንገድ መሰብሰባቸውን የተናገረው ሌላው የዚሁ ወረዳ ነዋሪ ወጣት ጀመል ናስር ነው፡፡


 

በቴክኖሎጂ ታግዞ የግብርና ሥራቸውን ማከናወናቸው ጊዜና ጉልበት እንደቆጠበላቸው ተናግሯል።

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በ2017/18 የመኸር ወቅት ከ563 ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ በተለያዩ ሰብሎች የለማ ሲሆን ከዚህም ከ54 ነጥብ 9 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይሰበሰባል ተብሎ እንደሚጠበቅ ከክልሉ ግብርና ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም