ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ለቱሪዝምና ለዱር እንሰሳት ጥበቃ ያለውን ምቹ ምህዳር በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 24/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ለቱሪዝምና ለዱር እንሰሳት ጥበቃ ያለውን ምቹ ምህዳር በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ስለሺ ግርማ ገለጹ።

የዓለም የዱር እንሰሳት ፕሮግራም ዓመታዊ ጉባኤ በአዲስ አበባ መካሄድ የጀመረ ሲሆን በጉባኤው ከተለያዩ ሀገራት የተወጣጡ ፖሊሲ አውጪዎችና የዘርፉ ባለሙያዎች እየተሳተፉ ነው።


 

የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ስለሺ ግርማ በጉባኤው መክፈቻ ኢትዮጵያ የሰው ዘርና የቡና መገኛ እንዲሁም የጥንታዊ ስልጣኔና የበርካታ ባህሎችና ቅርሶች ባለቤት ናት ብለዋል።

የኢትዮጵያ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ለቱሪዝምና ለዱር እንሰሳት ጥበቃ ምቹ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህንኑ ጸጋ በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን አስታውቀዋል።

በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የተተከሉ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞች ለብዝሃ ሕይወትና ለዱር እንሰሳት ጥበቃ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው ብለዋል።

ጉባኤው በዱር እንሰሳ ጥበቃ ላይ የተሻለ ተሞክሮ ያላቸው ሀገራት ልምዳቸውን የሚያካፍሉበትና በዘርፉ ያለው ትብብር የበለጠ የሚጠናከርበት እንደሚሆንም አንስተዋል።

የዓለም አቀፉ የዱር እንሰሳት ፕሮግራም ከፍተኛ ባለሙያ ሃና ፌርባክ ፕሮግራሙ ከ30 በላይ ሀገራት ላይ ከዱር እንሰሳት ጥበቃ ጋር የተያያዙ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

የዱር እንሰሳት በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ አደጋዎች እንዳይጠፉና እንዳይሰደዱ የሚደረገው ጥበቃና እንክብካቤ የበለጠ ሊጠናከር እንደሚገባም አንስተዋል።


 

በዓለም ባንክ የኢትዮጵያ፣ የኤርትራ፣ ሱዳንና ደቡብ ሱዳን የኦፕሬሽን ስራ አስኪያጅ ጁሊያና ቪክቶር በበኩላቸው፤ ለዱር እንሰሳት ተገቢውን ጥበቃ የሚያደርጉ ሀገራት ከቱሪዝም ዘርፉ በከፍተኛ ደረጃ ተጠቃሚ ናቸው ብለዋል።

ይሁንና ከዓለም ተለዋዋጭ ነባራዊ ሁኔታ አኳያ በዱር እንሰሳት ላይ የመጥፋት አደጋ መጋረጡን ጠቅሰው፤ በየቦታው የሚከሰቱ ግጭቶች የዱር እንሰሳት ከአካባቢያቸው እንዲሰደዱ እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።

ሀገራት ከዱር እንሰሳት ሀብታቸው ተገቢውን ጥቅም ለማግኘት ጥበቃውን ማጠናከር አለባቸው ሲሉም አሳስበዋል።

የዓለም አቀፉ የእንሰሳት ፕሮግራም ዓመታዊ ጉባኤ ዛሬን ጨምሮ ለአምስት ቀናት እንደሚካሄድ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም