የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የአራተኛ ሳምንት ተጠባቂ ጨዋታዎች - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የአራተኛ ሳምንት ተጠባቂ ጨዋታዎች
አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 24/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አራተኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ውሎ ሶስት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።
ከቀኑ 7 ሰዓት በአዲስ አበባ ስታዲየም ሀድያ ሆሳዕና ከኢትዮጵያ መድን ይጫወታሉ።
ሀድያ ሆሳዕና በሁለት ነጥብ 15ኛ ደረጃን ይዟል። የወቅቱ የሊጉ አሸናፊ ኢትዮጵያ መድን በአንድ ነጥብ 16ኛ ደረጃን ይዟል።
ኢትዮጵያን መድን በካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ ከግብጹ ፒራሚድስ ጋር በነበረው ጨዋታ ምክንያት የሁለተኛ እና ሶስተኛ ሳምንት ጨዋታዎቹ መራዘማቸው ይታወቃል።
ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ የመጀመሪያ ሶስት ነጥብ ለማግኘት ይጫወታሉ።
ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሸገር ከተማ ከቀኑ 10 ሰዓት በአዲስ አበባ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
በሊጉ ካደረጋቸው ሁለት ጨዋታዎች ስድስት ነጥብ ያገኘው ቅዱስ ጊዮርጊስ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው ሰባተኛ ደረጃን ይዟል።
አዲስ አዳጊው ሸገር ከተማ በሊጉ ካካሄዳቸው ሁለት ጨዋታዎች አንድ ነጥብ በማግኘት አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው 17ኛ ደረጃን ይዟል።
በዚሁ ዕለት በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም መቀሌ 70 እንደርታ ከሃዋሳ ከተማ ጋር ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
በሊጉ ባደረጋቸው ሶስት ጨዋታዎች አንድ ነጥብ ብቻ ያገኘው መቀሌ 70 እንደርታ 18ኛ ደረጃን ይዟል።
ተጋጣሚው ሃዋሳ ከተማ ከሶስት ጨዋታ ስድስት ነጥብ በመሰብሰብ አምስተኛ ደረጃን ይዟል።
መቀሌ 70 እንደርታ በሊጉ የመጀመሪያ ድሉን ለማግኘት ይጫወታል። ሃዋሳ ከተማ ካሸነፈ በሊጉ ሶስተኛ ድሉን ያስመዘግባል።