ቀጥታ፡

በሀገር ደረጃ የተወጠኑ ግዙፍ ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያን ዕድገት የሚያፋጥኑ ናቸው

ድሬዳዋ፤ ጥቅምት 23/2018 (ኢዜአ):-በሀገር ደረጃ የተወጠኑ ግዙፍ ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያን ኢኮኖሚያዊ  ዕድገት  በማፋጠን ወደ ላቀ ከፍታ የሚያሸጋግሩ መሆናቸውን በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሃብት መምህርና  ተመራማሪ ዘሪሁን ተምሳስ (ዶ/ር) ተናገሩ።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)  ጉባ ላይ ይፋ የተደረጉት ፕሮጀክቶች የሀገሪቷን የኢኮኖሚ መሠረቶች ወደ ብዝሃ ዘርፍ በማምጣት የተጀመረውን ሀገራዊ የብልፅግና ጉዞ በአስተማማኝ መንገድ ለማስቀጠል እንደሚያስችሉ ተመልክቷል።

በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሃብት መምህርና ተመራማሪ ዘሪሁን ተምሳስ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ መንግስት የወጠናቸው የልማት ስራዎች የሀገርን ከፍታ  የሚያረጋግጡ  ናቸው።

ወደ 30 ቢሊዮን ዶላር በጀት የሚፈጁት እነዚሁ ግዙፍ ፕሮጀክቶች በየትኛውም የሀገራችን ዘመን ያልተሞከሩና የሀገርን የለውጥና የዕድገት ጉዞ በአስተማማኝ መሠረት ላይ ለማዋቀር የሚያግዙ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ምሁሩ እንዳወሱት፤ በቢሾፍቱ የሚገነባው ግዙፉ የአውሮፕላን ማረፊያ፣የማዳበሪያ ፋብሪካ፣ የኒውክለር ማበልፀጊያ ፕላንት፣ የነዳጅ ማጣሪያና የጋዝ ፋብሪካን ጨምሮ ሌሎችም ፕሮጀክቶች የሀገርን ሁለንተናዊ እንቅስቃሴዎች ይበልጥ በማሳለጥ የዜጎችን ተጠቃሚነት በላቀ ደረጃ የሚያሳድጉ ናቸው።

በተጨማሪም የውጭ ምንዛሬን በማስቀረት እና በማስገኘት የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ለዋጋ ንረት መፍትሄ እንደሚያመጡ ነው ያመለከቱት። 

ፕሮጀክቶቹ ኢትዮጵያ ወደ ብዝሃ ዘርፍ ኢኮኖሚያዊ መዋቅር ለመሸጋገር የጀመረችውን ጉዞ ስኬታማ ለማድረግ መሰረት እንደሚጥሉም ተናግረዋል።

ይህም  ኢኮኖሚን  በማሳደግ   የህብረተሰቡን የልማት ተጠቃሚነት እንደሚያረጋግጥ  አክለዋል ።

እንደ ምሁሩ ማብራሪያ፤መንግስት  በሀገሪቱ ታሪክ  ግዙፍና አሻጋሪ ፕሮጀክቶች መጀመሩ የአሁንና የቀጣዩ ትውልድ ታላቅ ብስራትና ኩራት  ነው።

በመሆኑም እነዚህ አሻጋሪ ፕሮጀክቶች የሚፈለገውን ውጤት እንዲያስገኙ ዜጎች እና ምሁራን ልክ እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ   ሁሉ  ርብርባቸውን  እንዲያጠናክሩ መልእክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም