የጎንደር ከተማ ነጋዴዎች ለከተማቸው እድገትና ሰላም መስፈን በሚደረገው ጥረት የድርሻቸውን እየተወጡ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የጎንደር ከተማ ነጋዴዎች ለከተማቸው እድገትና ሰላም መስፈን በሚደረገው ጥረት የድርሻቸውን እየተወጡ ነው
ጎንደር ፤ ጥቅምት 23/2018 (ኢዜአ):-ለጎንደር ከተማ እድገትና ሰላምን ለማስፈን በሚደረገው ጥረት የድርሻቸውን እየተወጡ መሆናቸውን በጎንደር ከተማ የንግዱ ማህብረሰብ አባላት ገለጹ፡፡
በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮችና በአካባቢ ሰላምና ልማት ዙሪያ የከተማው የንግዱ ማህበረሰብ የምክክር መድረክ ዛሬ አካሂደዋል፡፡
ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል አቶ አብዱራህማን ሰኢድ ግብራቸውን በወቅቱ በመክፈል የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶች ዳር እንዲደርሱና ሰላምና ልማት እንዲረጋገጥ የበኩላቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።
በተለይም በአካባቢው የሰፈነውን ሰላም ለማጽናትና የህብረተሰቡን ሁለንተናዊ እድገት ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት መሳተፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።
ሌላው የውይይቱ ተሳታፊ አቶ ተሾመ ንጉሱ በበኩላቸው እንደ አንድ የንግዱ ማህበረሰብ አባል ህብረተሰቡን የሚያማርሩ ህገወጦችን በማጋለጥ መንግስት ለሰላም መስፈን የሚያደርገውን ጥረት ይበልጥ ለማገዝ እንደሚተጉ አስረድተዋል።
የንግዱ ማህበረሰብ የግብር ግዴታውን በመወጣት ለሀገር እድገት የሚያበረክተውን ሚና ማጠናከር እንደሚገባውም ጠቁመዋል።
በምንከፍለው ግብር የኮሪደር ልማትን ጨምሮ ሌሎች ፕሮጀክቶች መገንባታቸውን በማየታችን ተደስተናል፤ልማቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የድርሻዬን ለማበርከት ዝግጁ ነኝ ያሉት ደግሞ አቶ ጀማል ቃሲም ናቸው፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ገቢዎች መምሪያ ሃላፊ ወይዘሮ ጥሩዬ አታክልት እንደገለጹት በከተማው ሰላም መረጋገጡ የንግድ እንቅስቃሴው እንዲነቃቃ አስችሏል።
ይህም የንግዱ ማህበረሰብ ሰርቶ በሚያገኘው ልክ የመንግስትን ግብር በታማኝነትና በወቅቱ እንዲከፍል ምቹ መደላድል መፍጠሩን ተናግረዋል፡፡
የንግዱ ማህበሰረብም በሰላም ግንባታ እያበረከተ ያለውን ተሳትፎ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡
በምክክር መድረኩ ላይ የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ ከስድስት ክፍለ ከተሞች የተውጣጡ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት ተሳታፊ ሆነዋል፡፡