ቀጥታ፡

የምሽት ንግድ የሥራ ባህልን በማሳደግ የተሻለ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ፈጥሯል  

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 23/2018 (ኢዜአ):-የአዲስ አበባ ከተማ የምሽት ንግድ የአሰራር ሥርዓት የሥራ ባህልን በማሳደግ የተሻለ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ መፍጠሩን የከተማ አስተዳደሩ ንግድ ቢሮ ገለጸ።

በአዲስ አበባ ከተማ የተከናወኑ የኮሪደር ልማት ሥራዎች የነዋሪዎችን የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴ በማሳለጥ የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት እያሻሻለ ይገኛል።

በዚህም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት በደንብ ቁጥር 185/2017 የንግድና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እስከ ምሽት 3:30 አገልግሎት መስጠት እንዳለባቸው የሚደነግግ ውሳኔ ማሳለፉ ይታወቃል።

በመዲናዋ የተፈጠረው የምሽት ንግድና አገልግሎት የአሰራር ሥርዓትም በዘርፉ የተሰማሩ ዜጎችን የሥራ ባህል በማሻሻል ኢኮኖሚያዊ ገቢን እያሻሻለ እንደሚገኝ ይገለፃል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የንግድ ቢሮና ደንብ ማስከበር ባለስልጣን የስራ ኃላፊዎችም የመዲናዋን የምሽት ንግድና አገልግሎት አሰጣጥ ሂደት ተዘዋውረው ምልከታ አድርገዋል።


 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ የንግድ ሬጉላቶሪ ዘርፍ ምክትል ኃላፊ ስመኘው ተሾመ፥ በመዲናዋ የምሽት ንግድ አሰራር ሥርዓቶችን ባህል ማድረግ የሚያስችል ምቹ የመሠረተ ልማት ምኅዳር ተፈጥሯል ብለዋል።


 

የከተማ አስተዳደሩ ምክር ቤት የምሽት ንግድና አገልግሎት ደንብም የመዲናዋን የዲፕሎማቲክ ማዕከልነት የሚመጥን የምሽት ንግድና አገልግሎት ባህል እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል።

የመዲናዋ የኮሪደር ልማት የፈጠረው የምሽት ንግድ ባህልም የንግድ ሥርዓቱን በማዘመን በልምድና አርዓያነት የሚወሰድ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እንዲፈጠር ማድረጉን ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ምክትል ቢሮ ሀላፊ ጸጋዬ ደበሌ÷ የኮሪደር ልማት ለምሽት ንግድ የፈጠረው ዕድል የአገልጋዮችንና ተገልጋዮችን ተጠቃሚነት እያሳደገ ነው ብለዋል።


 

በመዲናዋ በንግድና አገልግሎት የተሰማሩ ተቋማት የከተማ አስተዳደሩን የምሽት ንግድና አገልግሎት ደንብ ተከትለው እንዲሰሩም ቀጣይነት ያለው ክትትልና ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

የምሽት ንግድ የአሰራር ሥርዓቱ በመዲናዋ ኢኮኖሚያዊ መነቃቃትን ፈጥሯል ያሉት ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደንብ ማስከበር ባለስልጣን ምክትል ስራ አስኪያጅ ከፍያለው ታደሰ ናቸው።


 

የመዲናዋን ንግድና አገልግሎት ለማሳለጥም እስከ ብሎክ አደረጃጀት ድረስ ከጸጥታ አካላት ጋር የተቀናጀ የድጋፍና ክትትል ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢዜአ ካነጋገራቸው ነጋዴዎች መካከል አስቴር ይታየው÷ የኮሪደር ልማት ለምሽት አገልግሎት ሰጪ ሱቆች የተለየ ውበት በማላበስ የህብረተሰቡን የግብይት ባህል እያሳደገ ነው ብለዋል።


 

ወጣት አብዱረዛቅ ኑር-ሁሴን በበኩሉ÷ የመዲናዋን የኮሪደር ልማት ተከትሎ ተግባራዊ የተደረገው የምሽት ንግድ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን እያሳደገ እንደሚገኝ ገልጿል።


 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም