ቀጥታ፡

በከተማው የተከናወነው የኮሪደር ልማት ምቹና ሳቢ ከባቢን ከመፍጠር ባለፈ አኗኗራችንን ቀይሯል-ነዋሪዎች

ይርጋጨፌ ፤ ጥቅምት 23/2018 (ኢዜአ):- በጌዴኦ ዞን በይርጋ ጨፌ ከተማ የተከናወነው የኮሪደር ልማት ምቹ ውብና ሳቢ ከባቢን ከመፍጠር ባለፈ የአኗኗር ዘይቤያቸው እንዲቀየር ማድረጉን የይርጋ ጨፌ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።

በከተማው 2 ነጥብ 7 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የአስፋልት ግንባታን ያካተተ የሶስተኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት ስራን ለማስጀመር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑም ተመላክቷል።

በዚህም ባለፉት ሁለት ምዕራፎች የተከናወኑ የኮሪደር ልማት ስራዎች የአኗኗር ዘይቤያቸውን እንደቀየረ ነው አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ነዋሪዎች የተናገሩት።


 

በተለይ በከተማዋ ከዚህ ቀደም ቆሻሻ መጣያ የሆኑ ለተለያዩ ተላላፊ በሽታዎችና ለወንጀል ድርጊቶች መነሻ የነበሩ ስፍራዎች ዛሬ ላይ ለምተው ውብ ወደሆኑ መናፈሻዎችና መዝነኛ ስፍራነት ተቀይረዋል ብለዋል።

ይህም የከተማዋን ገጽታ ከመቀየሩ ባለፈ በዚህ ተሰማርተው በርካቶች የኢኮኖሚ ተጠቃሚ እየሆኑ እንዲሁም በትርፍ ጊዜያቸው ከቤተሰብ ጋር የሚዝናኑበትና የሚናፈሱበት ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ገልጸዋል።

አስተያየታቸውን ከሰጡት መካከል የከተማው ነዋሪ መጋቢ ከበደ ይርባዬ የኮሪደር ልማት የከተማዋን እድገት ከማፋጠን ባለፈ የአኗኗር ዘይቤያቸውን እንደቀየረ ተናግረዋል።


 

ከዚህ ቀደም በከተማው የማረፊያና የመናፈሻ ቦታ ባለመኖሩ በግልም ሆነ በቤተሰብ ደረጃ እንቅስቃሴ ለማድረግ የማይታሰብ እንደነበር ነው ያነሱት።

ይሁንና የኮሪደር ልማት በከተማዋ ከሶስት በላይ ቆሻሻ ስፍራዎችን ወደ መዝናኛ ቦታ መቀየሩን ተከትሎ የመናፈስና በጋራ በእግር በመጓዝ ጊዜን ለማሳለፍ እድል መፍጠሩን ተናግረዋል።

የኮሪደር ልማት በጽዱና በውብ ስፍራዎች የስራ እድል እንዲፈጠርልን ምክንያት ሆኗል የምትለው ደግሞ ወጣት እምነት ንጉሴ ማራኪና ለዐይን ሳቢ ሆኖ የተሰራ በመሆኑ ልዩ ስሜትን ይፈጥራል ብላለች።


 

በኮሪደር ልማት በተገነባው ካፍቴሪያ እሷን ጨምሮ አምስት ወጣቶች ወደ ስራ ገብተው ራሳቸውን ከመቻል ባለፈ በጽዱ አካባቢ ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት እንዲያቀርቡ ለማድረግ እንደቻሉም ተናግራለች።

ምክትል ኢንስፔክተር ግርማ ታደሰ በበኩላቸው የኮሪደር ልማት ደህንነቱ በተጠበቀ ምቹና ጽዱ አካባቢ የመኖር ልምድን እያጎለበት ነው ብለዋል።


 

በተለይ የወንጀል ድርጊት ይፈፀምባቸው የነበሩ አካባቢዎችን ወደ አረንጓዴና ብርሃናማ ስፍራነት በመቀየር ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዲኖር ማስቻሉን ጠቁመዋል።

በኮሪደር ልማት ከ17 ነጥብ 6 ኪሎ ሜትር በላይ የመንገድ ፕላን በማስጠበቅ ከተማዋ ሁሉን አቀፍ ልማት እንድታከናውን ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን የከተማ አስተዳደሩ ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ዳዊት ታምራት ተናግረዋል።


 

በተጨማሪውም 2 ነጥብ 6 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የእግረኛ መንገድ፣ አረንጓዴ ስፍራዎችና ካፍቴሪያዎችን ያካተተው የኮሪደር ልማት ለነዋሪዎች ማረፊያና የስራ እድል መፍጠሪያ ማዕከል መሆኑንም አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም