ቀጥታ፡

በክልሉ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶችን ተደራሽነት በማሳደግ ብቁና ተወዳዳሪ ዜጋን ለማፍራት ትኩረት ተሰጥቷል

ቦንጋ፤ ጥቅምት 23/2018 (ኢዜአ)፦ በክልሉ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ በማሻሻልና የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ተደራሽነትን በማሳደግ ብቁና ተወዳዳሪ ዜጋን ለማፍራት በትኩረት እየሰራ መሆኑን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አልማ ዘውዴ እንደገለፁት፤ በክልሉ የትምህርት ጥራትን በማረጋገጥ ብቁና ተወዳዳሪ ዜጋ ለማፍራት ለቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ተደራሽነትና የትምህርት ቤቶችን  ደረጃ ለማሻሻል ትኩረት ተሰጥቷል።

ለዚህም በወረዳዎችና በከተማ አስተዳደሮች ሞዴል የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች በግንባታ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።


 

በእስካሁኑ ሂደት ከ92 ሚሊዮን 24 ሺህ ብር በላይ በሆነ ወጪ ግንባታቸው ከተጀመሩ 42 ትምህርት ቤቶች መካከል 26ቱ  ተጠናቀው የመማር ማስተማር ስራ መጀመራቸውን ተናግረዋል።

የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻልም የትምህርት ለትውልድ ንቅናቄን በማጠናከር በበጀት ዓመቱ ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ  ርብርብ እየተደረገ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

በአንደኛው ሩብ ዓመት በካሽ፣ በዓይነትና በጉልበት ከ202 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ሀብት መሰብሰብ መቻሉን ገልፀዋል። 

የካፋ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሙሉጌታ መሸሻ በበኩላቸው በዞኑ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የቅድመ አንደኛ ትምህርት ቤቶችን በመገንባትና ምቹ  የመማሪያ አካባቢን መፍጠር ላይ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።


 

በዚህም በዞኑ በሚገኙ 17 ወረዳዎችና የከተማ አስተዳደር መዋቅሮች አንዳንድ ሞዴል ቅድመ አንደኛ ትምህርት ቤቶችን የመገንባት ስራ እየተሰራ  መሆኑን ተናግረዋል።

የተለያዩ አካላትን በሰፊው በማሳተፍ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል የትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉንም ገልጸዋል።

በህብረተሰቡ ተሳትፎ የትምህርት ስራን ውጤታማ ለማድረግ  በሚደረገው ጥረት  የበኩላቸውን እየተወጡ መሆናቸውን  የገለጹት ደግም የቦንጋ ከተማ 03 ቀበሌ ነዋሪ  አቶ ፍቅሬ ገብረየሱስ እና አቶ ኢጃራ በዳኔ ናቸው። 


 

የትምህርት  ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል  በተጀመረው ተግባርም የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፋቸውን አጠናክረው መቀጠላቸውን አስረድተዋል።


 

በግላቸው ከሚያደርጉት አስተዋፅኦ ባሻገር ሌሎችንም በማስተባበር ሚናቸውን በመወጣት ላይ መሆናቸውን ጠቁመው እያደረጉት ያለውን አስተዋፅኦም አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም