በአስተዳደሩ አንድ ሺህ 300 ዘመናዊ የማገዶ ቆጣቢ ምድጃዎች እየተሰራጩ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአስተዳደሩ አንድ ሺህ 300 ዘመናዊ የማገዶ ቆጣቢ ምድጃዎች እየተሰራጩ ነው
ሰቆጣ ፤ ጥቅምት 23/2018 (ኢዜአ):-በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ባለፉት ሶስት ወራት አንድ ሺህ 300 ዘመናዊ የማገዶ ቆጣቢ ምድጃዎችን በማምረት ለአርሶ አደሮች እንዲሰራጩ እየተደረገ መሆኑን የብሔረሰብ አስተዳደሩ ውሃና ኢነርጂ መምሪያ አስታወቀ።
በመምሪያው የተሻሻሉ ማገዶ ቆጣቢ ቴክኖሎጂዎች ልማት ማስፋፊያ ባለሙያ አቶ ሃብቱ ታከለ ለኢዜአ እንደገለጹት አማራጭ ኢነርጂን ተደራሽ በማድረግ የአርሶ አደሩን አኗኗር ዘይቤ ለመለወጥ በትኩረት እየተሰራ ነው።
የማገዶ ቆጣቢ ምድጃ ስርጭቱ የደን ጭፍጨፋን ለመቀነስ፣ የእናቶችን ጤና ለመጠበቅና ለእንጨት ለቀማ የሚያውሉትን ጊዜና ጉልበት ለሌሎች የልማት ስራዎች ለማዋል የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም በያዝነው በጀት ዓመት ሶስት ሺህ 970 የተሻሻሉ የማገዶ ቆጣቢ ምድጃዎችን ለአርሶ አደሮች ለማሰራጨት ታቅዶ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ባለፉት ሶስት ወራት ብቻ አንድ ሺህ 300 የማገዶ ቆጣቢ ምድጃዎችን በማስመረት 650 የሚሆነውን ለአርሶ አደሩ ማሰራጨት መቻሉን ተናግረዋል።
ዞኑ አጋር አካላትን በማስተባበር በዝቋላ፣ አበርገሌ ሰቆጣ ዙሪያና ፃግብጅ ወረዳዎች የተሻሻለ የማገዶ ቆጣቢ ምድጃዎችን በአካባቢው በማስመረት ተደራሽነቱን ለማሳደግ እየሰራ ነው ብለዋል።
በአበርገሌ ወረዳ የ01 ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ መድን ህሉፍ እንዳሉት ዘመናዊ የማገዶ ቆጣቢ ምድጃ መጠቀም በመቻላቸው ከጭስና ተያይዘው ከሚመጡ ችግሮች እንደተላቀቁ ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም ለማብሰያነት የምንጠቀመው በአካባቢያችን የሚገኙ ዛፎችን በመቁረጥ ነበር ያሉት ወይዘሮ መድን ዘመናዊ የማገዶ ቆጣቢ ምድጃ መጠቀማቸው ዛፍ ከመቁረጥ እንዲታቀቡ እንዳደረጋቸው ገልጸዋል።
ሌላዋ የወረዳው ነዋሪ ወይዘሮ ሚኬዔሉ መንግስቱ በበኩላቸው የዘመናዊ የማገዶ ቆጣቢ ምድጃ እንጨት ለመልቀም የሚያሳልፉትን ጊዜና ጉልበት እንደቆጠበላቸው ተናግረዋል።
ለአካባቢው ማህበረሰብ የማገዶ ቆጣቢ ምድጃ ያለውን ጥቅም በማስረዳት የበኩሌን ልምድ እያካፈልኩ እገኛለሁ ብለዋል።