ቀጥታ፡

የዲጂታል መታወቂያ በተለያዩ አካባቢዎች ለማዳረስ የሚያስችል የአገልግሎት ማዕከላትን የማስፋት ስራ እየተከናወነ ነው

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 23/2018 (ኢዜአ):-የዲጂታል መታወቂያ አገልግሎትን በተለያዩ አካባቢዎች ለማዳረስ የሚያስችል የአገልግሎት ማዕከላት ማስፋት ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም የምዝገባ አስተባባሪ ደጀኔ ገብሬ ገለጹ፡፡

እስካሁን ከ27 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ለፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ተመዝግበዋል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም የምዝገባ አስተባባሪ ደጀኔ ገብሬ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤   ለሁሉም ነዋሪዎች ዲጂታል መታወቂያን በቀላሉ ተደራሽ ለማድረግ ሰፋፊ ተግባራት እየተከናወኑ ነው።

የምዝገባ አገልግሎቱን በተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች ለማዳረስ ከአጋር ተቋማት ጋር በመተባበር የአገልግሎት ማዕከላት በማስፋት ምዝገባ እያካሄደ ነው።

በተጨማሪም አገልግሎቱ ወደ ሩቅ አካባቢዎች እንዲደርስ በተንቀሳቃሽ የምዝገባ ጣቢያዎች (Mobile Registration Units) አማካኝነት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። 

በአሁኑ ወቅት ከአምስት ሺህ በላይ የመመዝገቢያ ማሽኖች አገልግሎት ላይ ናቸው ያሉት አስተባባሪው፤ ከ27 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ለፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ተመዝግበዋል ብለዋል።

እስከ በጀት ዓመቱ አጋማሽ ድረስ የመመዝገቢያ ማሽኖቹን ቁጥር ወደ 10 ሺህ በማሳደግ ተደራሽነትን ለማስፋት መታቀዱን ገልጸዋል። 

በአጠቃላይ በዓመቱ ውስጥ 60 ሚሊዮን ዜጎችን ለመመዝገብ ዕቅድ የተያዘ ሲሆን፤ ይህንኑ ለማሳካት ጠንካራ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን አስተባባሪው አስረድተዋል።

የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ የዲጂታል ኢኮኖሚውን በማሳደግ፣ የገንዘብ ማጭበርበርን በመቀነስ እንዲሁም የመንግሥትና የግል አገልግሎቶችን ይበልጥ ቀልጣፋና ግልጽ በማድረግ ረገድ ትልቅ ሚና እንደሚጫወት ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም