የሰላምን አማራጭ ያልተከተሉ አካላት የመንግስትን የሰላም ጥሪ በመቀበል ልዩነቶችን በውይይት ለመፍታት ዝግጁ መሆን አለባቸው - ኢዜአ አማርኛ
የሰላምን አማራጭ ያልተከተሉ አካላት የመንግስትን የሰላም ጥሪ በመቀበል ልዩነቶችን በውይይት ለመፍታት ዝግጁ መሆን አለባቸው
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 23/2018 (ኢዜአ):- የሰላምን አማራጭ ያልተከተሉ አካላት የመንግስትን የሰላም ጥሪ በመቀበል ልዩነቶችን በውይይት ለመፍታት ዝግጁ መሆን እንዳለባቸው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ተናገሩ፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን ሁለተኛ መደበኛ ስብሰባ ወቅት እንዳረጋገጡት፤ መንግሥት ወደ ሰላም ከሚመጣ የትኛውም ኃይል ጋር ለመታረቅ ብቻ ሳይሆን አብሮ ለመስራት ሁል ጊዜም ዝግጁ ነው።
በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ የሚስተዋሉ የሰላምና የፀጥታ ችግሮች በዘላቂነት እንዲፈቱ መንግሥት ሰላምን ቀዳሚ አማራጭ አድርጎ እየሠራ መሆኑንም ነው የተናገሩት።
መንግስት ሁሌም የሰላም መንገድ ከሚመርጡት ጋር ለመነጋገር ዝግጁ መሆኑን በድጋሚ አረጋግጠው፤ በአገር ፍላጎት እስከ ተግባባን ድረስ የግል ጉዳይን መተው አስፈላጊ ነው ብለዋል።
አሁንም ለሰላም በራችን ክፍት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ካልተደመርንና ካልተጋገዝን የኢትዮጵያን ችግሮች በአጭር ጊዜ ልንፈታ እንደማንችል በመገንዘብ በሰላማዊ መንገድ አብሮ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።
ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ፈቲህ ማህዲ (ዶ/ር)፤ችግሮችን በውይይት መፍታት ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ተግባር ነው ብለዋል።
መንግስት ለታጠቁ ኃይሎች ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪዎችን እያቀረበ መሆኑን ገልጸው፤ ጥሪውን ተቀብለው ወደ ሰላማዊ አማራጭ የመጡ በርካታ ወገኖች መኖራቸውን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ አሁን ላይ በፈጣን ዕድገት ላይ እንደምትገኝ ጠቁመው፤ ሀገሪቷ ከምታደርገው የዕድገት ግስጋሴ የሚያስተጓጉላት ነገር ባለመኖሩ ታጣቂዎች ግብ ለሌለው ትግል ጊዜያቸውን ማባከን እንደሌለባቸው አብራርተዋል።
መንግስት ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠር እና ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት የብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን በማቋቋም ችግሮች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ገልጸዋል።
በምክክሩ ማንኛውም አካል አለኝ የሚለውን ጥያቄ በማቅረብ በሰላማዊ መንገድ መወያየት እንደሚችል አመልክተዋል።
ሌላኛዋ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል አስቴር ከፍታው በበኩላቸው፤ አሁን ላይ ቡድኖችንም ሆነ ግለሰቦችን ለትጥቅ ትግል የሚዳርግ ምንም ሁኔታ እንደሌለ ገልጸዋል።
የፖለቲካ ልዩነት ያላቸውም ሆኑ የታጠቁ ኃይሎች ለሰላማዊ ውይይት ቅድሚያ በመስጠት ለዘላቂ ሰላም እውን መሆን የበኩላቸውን ድርሻ ማበርከት እንዳለባቸው ተናግረዋል።
በትጥቅ የተደገፈ ትግል ሲያደርጉ የነበሩ ኃይሎች የመንግስትን የሰላም ጥሪ ተቀብለው በመግባት በልዩ ልዩ የስራ ዘርፎች ተሰማርተው አገራቸውንና ህዝባቸውን እያገለገሉ ይገኛሉ።