ቀጥታ፡

ዕውቀታችንን በማጎልበት የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ የሚያስችል እድል ተፈጥሮልናል-የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ተፈታኞች

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 23/2018(ኢዜአ)፡- ዕውቀታቸውን በማጎልበት የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ የሚያስችል እድል እንደተፈጠረላቸው የአዲስ አበባ ከተማ የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ገለጹ። 

የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ የመሰናዶ ትምህርት ደረጃ ተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና ማላቂያ ስትራቴጂ ተግባራዊ ማድረጉ ይታወቃል።

ኢዜአ የስትራቴጂ ትግበራው በመሰናዶ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ላይ የሚኖረውን ፋይዳ አስመልክቶ የመዲናዋን የመማር ማስተማር ተዋናዮችን አነጋግሯል።

በኮከበ ፅባህ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል የማህበራዊ ሳይንስ ተማሪ ሴማዊት ኤርሚያስ፤ ስትራቴጂው የመማር ማስተማር ሥርዓቱን በማሻሻል የተሻለ የዝግጅት አቅም እየፈጠረልን ነው ብላለች።


 

አዲሱ የትምህርት መርሃ ግብር ለቀጣዩ ሀገር አቀፍ መልቀቂያ ፈተና ዝግጅት ጉልህ እገዛ እያደረገልን ነው ያለው ደግሞ ሌላኛው የትምህርት ቤቱ የ12ኛ ክፍል የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪ አላዶር ደምሴ ነው።


 

የብርሃን ጉዞ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል የማህበራዊ ሳይንስ ተማሪ ትንሳኤ ገላና፤ ስትራቴጂው ያለፉባቸውን የትምህርት እርከኖች ዕውቀት እያሻሻለላቸው መሆኑን ተናግራለች።


 

በተለይም ቀጣይ የሚወስዱትን የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ የእርስ በእርስ መማማር ዝግጅታቸውን እያዳበረላቸው እንደሚገኝ ገልጻለች።

ሌላኛዋ የትምህርት ቤቱ የ12ኛ ክፍል የማህበራዊ ሳይንስ ተማሪ መዓዛ ከበደ፤ በአዲስ መልክ ተግባራዊ የተደረገው የትምህርት መርሃ ግብር እራሳችንን እንድናበቃ እያስቻለን ነው ብላለች።


 

በኮከበ ፅባህ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪ ፋሲካ ዘሪሁን፤ አዲሱ የትምህርት መርሃ ግብር የተሻለ የመማር ማስተማር ምኅዳር እንደፈጠረላቸው ገልጿል።

የብርሃን ጉዞ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ምክትል ርዕሰ መምህር መኮንን ሙሉጌታ፤  የፈተና ማላቂያ ስትራቴጂው ተማሪዎች የማጠናከሪያ ትምህርት የሚወስዱበትን ወሳኝ ዕድል ፈጥሯል ብለዋል።


 

ስትራቴጂው የትምህርት ጥራትና የተማሪዎችን ዕውቀት በማሻሻል ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እያበረከተ ነው ያሉት ደግሞ የኮከበ ፅባህ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ምክትል ርዕሰ መምህር ሙሉዓለም ኃይሉ ናቸው።


 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዘላለም ሙላቱ (ዶ/ር)፤ የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና ማላቂያ ስትራቴጂ ተግባራዊ መደረጉን ገልጸዋል።


 

ስትራቴጂውም ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ያሉ የትምህርት ዓይነቶችን በመደበኛ እና ተጓዳኝ የመማር ማስተማር ውጤታማነትን የሚያሻሽል የማስፈጸሚያ ስልቶች ታግዞ ስራ ላይ መዋሉን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም