"ሮድ 2029" የተሰኘው የታዳጊዎች እግር ኳስ የስልጠና ፕሮጀክት ግቡን ማሳካት በሚያስችል እንቅስቃሴ ላይ ነው - ኢዜአ አማርኛ
"ሮድ 2029" የተሰኘው የታዳጊዎች እግር ኳስ የስልጠና ፕሮጀክት ግቡን ማሳካት በሚያስችል እንቅስቃሴ ላይ ነው
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 23/2018(ኢዜአ)፡- "ሮድ 2029" የታዳጊዎች እግር ኳስ የስልጠና ፕሮጀክት ግቡን ማሳካት በሚያስችል እንቅስቃሴ ላይ መሆኑን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ባህሩ ጥላሁን ገለጹ።
ኢትዮጵያ የ2029ን የአፍሪካ ዋንጫ ለማዘጋጀት ጥያቄ ማቅረቧ ይታወሳል፡፡
በዚህም ውድድር ኢትዮጵያን ወክሎ የሚሳተፍ ጠንካራና አሸናፊ ብሔራዊ ቡድን መገንባት የሚያስችል "ሮድ 2029" የታዳጊዎች እግር ኳስ የስልጠና ፕሮጀክት ተጀምሯል፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ባህሩ ጥላሁን ለኢዜአ እንዳሉት፤ "ሮድ 2029"ን ለማሳካት ከኢትዮጵያ ከሁሉም አካባቢዎች 85 ብቃት ያላቸው ታዳጊዎች ተመርጠው ለዘጠኝ ወራት ስልጠና ወስደው ብቃት ያላቸው ተመርጠዋል፡፡
ከእነዚህ ታዳጊዎች መካከል 26ቱ በብቃታቸው ተመርጠው የ"ሮድ 2029" ግብን ማሳካት የሚያስችል የክፍል ውስጥ እና የሜዳ ላይ ስልጠና እየወሰዱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ታዳጊዎቹ ኢትዮጵያ በመጭው ህዳር በምታስተናግደው ከ17 ዓመት በታች የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ የእግር ኳስ ማህበር ምክር ቤት ዞን እንደሚሳተፉ ተናግረዋል፡፡
ይህ የአጭር ጊዜ ግብ መሆኑን የጠቀሱት ዋና ሥራ አስፈፃሚው፤ ኢትዮጵያ በ2029 ለማስተናገድ ላቀረበቸው የአፍሪካ ዋንጫ ዝግጅት ስንቅ የሚሆን ነው ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በ2029 የአፍሪካ ዋንጫ ላይ በአሸናፊነት መሳተፍ የሚያስችል አቅም እንዲገነባ ታስቦበት የተጀመረው "ሮድ 2029" ፕሮጀክት በተሳካ ሁኔታ እየሄደ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
"ሮድ 2029" የታዳጊዎች እግር ኳስ የስልጠና ፕሮጀክት በአሜሪካዊ እና ኢትዮጵያዊ አሰልጣኞች ጥምረት የሚካሄድ መሆኑን የገለጹት ዋና ሥራ አስፈፃሚው፤ በኢትዮጵያ ዓለም የደረሰበትን ዘመናዊ ሥልጠና እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።
በዲጂታል አማራጮች ተደግፎ በንድፈ ሀሳብና በተግባር የሚሰጥ ሥልጠና መሆኑን በማንሳት፤ በእስካሁኑ ሂደት ተስፋ ሰጭ ውጤት እንደታየበት ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የ2029 የአፍሪካ ዋንጫ ለማዘጋጀት እንድትመረጥ የቴክኒክ ጉዳዮችን ጨምሮ የተለያዩ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡