በኢትዮጵያ የተጀመሩ ሜጋ ፕሮጀክቶች የሀገሪቱን የማንሰራራት ጉዞ የሚያረጋግጡ ናቸው-ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ የተጀመሩ ሜጋ ፕሮጀክቶች የሀገሪቱን የማንሰራራት ጉዞ የሚያረጋግጡ ናቸው-ምሁራን
ሆሳዕና፤ጥቅምት 22/2018 (ኢዜአ) ፡- የተጀመሩ ሀገራዊ ሜጋ ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያን የማንሰራራት ጉዞ እውን ለማድረግ ጠቀሜታቸው የጎላ መሆኑን የዋቸሞ ዩኒቨርሰቲ ምሁራን ገለፁ።
የዘመናት ቁጭት የሆነው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በተጠናቀቀ ማግስት በሶማሌ ክልል ካሉብ በዓመት 111 ሚሊዮን ሊትር ማምረት የሚችለውን የኦጋዴን ፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ ማምረቻ ተመርቆ የሁለተኛ ዙር ፕሮጀክት ግንባታ ሥራ መጀመሩ የሚታወስ ነው።
መንግስት በበጀት ዓመቱ የኒኩሌር ፕላንት፣ የማዳበሪያ ፋብሪካ፣ የነዳጅ ማጣሪያ፣ ግዙፍ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አየር ማረፊያን ጨምሮ ሜጋ ፕሮጀክቶች ግንባታ መጀመሩ ይፋ ማድረጉ ይታወቃል፡፡
እነዚህ የልማት ፕሮጀክቶች ለሀገራዊ እድገት መፋጠን ያላቸውን ፋይዳ በተመለከተ ኢዜአ ያነጋገራቸው የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን የተጀመሩ ሀገራዊ ሜጋ ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያን የማንሰራራት ጉዞ እውን ለማድረግ ጉልህ ጠቀሜታ ያላቸው ናቸው።
በዩኒቨርሲቲው የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ትምህርት ክፍል መምህር ጌታሁን አበራ ኢትዮጵያውያን ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶችን በራሳቸው አቅም መገንባት እንደሚችሉ በሕዳሴው ግድብ ማሳየታቸውን አስታውሰዋል።
ይህም ሌሎች ሜጋ ፕሮጀክቶችን በራስ አቅም ማሳካት እንደሚቻል ጥሩ ማሳያ መሆኑን ገልጸው፣ መንግስት በቅርቡ ይፋ ያደረጋቸው ሀገራዊ የልማት ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያ የማንሰራራት ጉዞ አይቀሬ መሆኑን የሚያረጋግጡ ናቸው ብለዋል።
እየታየ ያለው ሁለንተናዊ የዕድገት ጉዞና የተጀመሩ የልማት ዕቅዶች ኢትዮጵያን ወደቀደመ ክብሯ ከመመለስ ባለፈ የመደራደር እና የተደማጭነት አቅሟን እንደሚያሳድገውም መምህር ጌታሁን አንስተዋል፡፡
ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ጸጋዎች የተቸረች ብትሆንም ጸጋዎችን በራስ አቅም አልምታ መጠቀም ላይ ችግሮች እንደነበሩ አስታውሰዋል።
ለዚህም የውጭና የውስጥ ተጽዕኖ እና ለልማት ቁርጠኛ አለመሆናችንን እንደእንድ ምክንያት የጠቀሱት መምህሩ፣ በአሁኑ ወቅት መንግስት ሀገርን ለማልማት ያለውን ጽኑ ፍላጎት በተግባር እያሳየ መሆኑን ተናግረዋል።
በቅርቡ የተጀመሩና የሀገርን የማንሰራራት ጉዞ የሚያረጋግጡ ሜጋ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለአገልግሎት እንዲበቁ ዜጎች በገንዘብ፣ በሀሳብና ሰላምን በማጽናት ድጋፍ ማድረግ እንዳለባቸውም ገልጸዋል።
በዩኒቨርሲቲው የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ሙሉአለም ኃይለማርያም በበኩላቸው መንግስት በተለያዩ ችግሮች ውስጥ ለማመን የሚከብዱ ታላላቅ የልማት ሥራዎችን ማከናወኑን አድንቀዋል፡፡
በተለይ በቅርቡ ያስጀመራቸው ሜጋ ፕሮጀክቶች ሲጠናቀቁ የኢትዮጵያን የቀጣይ እጣ ፈንታ የሚወስኑ፣ የተሻለ የሚያደርጉና ዓለም አቀፍ ተሰሚነቷን የሚያሳድጉ ናቸው ብለዋል።
የልማት ፕሮጀክቶቹን ለስኬት በማብቃት እያደገ ከመጣው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ጋር በማስተሳሰር የዜጎችን ተጠቃሚነት ወደላቀ ደረጃ ማሳደግ እንደሚቻል ገልጸው፣ ፕሮጀክቶቹ የሀገርን የመደራደር አቅም ከፍ ያደርጋሉ ብለዋል።
እንደ መምህር ሙሉአለም ገለጻ ፕሮጀክቶቹ በታሰበው የጊዜ ገደብ ተጠናቅቀው ለአገልግሎት እንዲበቁ በሕዳሴው ግድብ የታየው አንድነትና ትብብር ሊጠናክር ይገባል።
በሀገር ልማትና ብሔራዊ ጥቅም ልዩነት ሊኖረን አይገባም ያሉት መምህሩ፣ ለዚህም ከመንግስት ጋር ተቀናጅቶና ተባብሮ መስራት እንደሚገባ ነው የገለጹት።
በተለይ ውስጣዊ አንድነትን ማጠናከር የዚህ ትውልድ አደራ መሆን እንዳለበት ነው ያስገነዘቡት።