ወጣቱ በመልካም ስብዕና ታንጾ በልማትና በሰላም ግንባታ ተሳትፎውን እንዲያጠናክር በቅንጅት መስራት ይጠበቅበታል - ኢዜአ አማርኛ
ወጣቱ በመልካም ስብዕና ታንጾ በልማትና በሰላም ግንባታ ተሳትፎውን እንዲያጠናክር በቅንጅት መስራት ይጠበቅበታል
ጋምቤላ፤ ጥቅምት 22/2018(ኢዜአ)፦ ወጣቱ በመልካም ስብዕና ታንጾ በሀገር ልማትና በሰላም ግንባታ ተሳትፎውን እንዲያጠናክር በቅንጅት መስራት እንደሚጠበቅበት ተገለጸ።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከጋምቤላ ክልል ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ቢሮ ጋር በመተባበር በወጣቶች የሰላምና ደህንነት ብሔራዊ የድርጊት መርሃ ግብር ዙሪያ የምክክር መድረክ በጋምቤላ ከተማ አካሂዷል፡፡
የኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤት ፕሬዘዳንት ፉአድ ገና በመድረኩ እንዳለው ወጣቶች በልማትና በሰላም ግንባታ ያላቸውን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማጎልበት በርካታ ጥረቶች እየተደረጉ ይገኛሉ፡፡
በዚህም ባለፉት የለውጥ አመታት ወጣቱ በሀገሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች ላይ ቀጥተኛ ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆን በተከናወኑ ተግባራት አመርቂ ውጤት መመዝገቡን ተናግሯል፡፡
ወጣቱን በሁሉም መስክ ማሳተፍ አንደ ሀገር የምንመኘውን ብልፅግና እውን ለማድረግ የጎላ አበርክቶ እንዳለውም አብራርቷል።
በተለይም የወጣቱን ስብዕና በመገንባት ረገድ የተጀመሩ ጥረቶች ይበልጥ እንዲጠናከሩ በቅንጅት መስራት እንደሚገባ ገልጿል።
የመድረኩ አላማም የወጣቶችን ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ እንደ ሀገር የተነደፈውን የሰላምና ደህንነት ብሄራዊ የድርጊት መርሃ ግብር በሁሉም አካባቢዎች ተግባራዊ ማድረግ ነው ብሏል።
በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የወጣቶች ተሳትፎና አደረጃጀት የአቅም ግንባታ ዴስክ ኃላፊ አድነው አበራ በበኩላቸው ወጣቱን በመልካም ስነ ምግባር ቀርጾ በሀገር ግንባታ ሂደቱ ላይ ያለውን ተሳትፎ ለማጠናከር በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
በተለይም ወጣቱ ዋነኛ የልማት አቅም መሆኑን በመረዳት በሁሉም የልማት መስኮች በባለቤትነት እንዲሳተፉ እየተደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
መንግስት ወጣቱን ለማብቃት ከሚያደረገው ጥረት በተጓዳኝ ወጣቱ ያለውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ራሱን ለመለወጥ መዘጋጀት እንዳለበትም አስገንዝበዋል፡፡
የጋምቤላ ክልል ወጣቶች ምክር ቤት ጸሐፊ ወጣት ሰለሞን አሰፋ፣ ወጣቱ ትርጉም ባለው ሁኔታ የተሳተፈበት የልማትና የሰላም ግንባታ ሂደት ውጤታማ ይሆናል ብሏል፡፡
በምክክር መድረኩ የወጣት አደረጃጀትና ማህበራት ተወካዮች፤ የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች ተገኝተዋል።