ኢትዮጵያ በታዳሸ ሀይል እያከናወነቻቸው ያሉ ተግባራት የኢንዱስትሪ ምርቶቿን ተወዳዳሪነት ያሳድገዋል - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በታዳሸ ሀይል እያከናወነቻቸው ያሉ ተግባራት የኢንዱስትሪ ምርቶቿን ተወዳዳሪነት ያሳድገዋል
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 22/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በታዳሸ ሀይል እያከናወነቻቸው ያሉ ተግባራት የኢንዱስትሪ ምርቶቿን ደረጃ ከፍ በማድረግ በአውሮፓ ገበያ ተወዳዳሪነቷን ማሳደግ እንደሚያስችላት በኢትዮጵያ የጀርመን ተጠባባቂ አምባሳደር ፈርዲናንድ ቮን ዌይ ገለጹ።
ተጠባባቂ አምባሳደሩ እንደተናገሩት፤ በኢትዮጵያ በኢኮኖሚው ዘርፍ እየተደረጉ ያሉ ማሻሻያዎች የሚበረታቱ ናቸው።
እነዚህ ስራዎችም ከዲጂታላይዜሽን እና ፈጠራ ጋር ተያይዘው የሚሄዱ መሆናቸውን አመልክተዋል።
በሀገሪቱ እየተከናወኑ ያሉ የኢኮኖሚ ለውጦች ለወጣቶች፣ ለፈጠራ ባለሙያዎች ሃሳባቸውን በትክክል ወደ ተግባር መለወጥ የሚያስችል መሆኑንም ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ ለታዳሽ ኃይል የሰጠችው ትኩረት የሚደነቅ መሆኑን ገልጸው የውሃ፣ የንፋስ፣ የጂኦተርማል እና የፀሐይ ኃይል አስፈላጊ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ በታዳሸ ሀይል እያከናወነቻቸው ያሉ ስራዎች የኢትዮጵያን የኢንዱስትሪ ምርቶች ተወዳዳሪነት በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያሳድገው ተናግረዋል።
ከእነዚህ የሀይል ምንጮች የሚወጡ ምርቶች በአውሮፓ ገበያ ላይም ተወዳዳሪነታቸውን እንደሚጨምር ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ እና ጀርመን በርካታ ዓመታት ያስቆጠረ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዳላቸው አመልክተው፤ የሁለቱ ሀገራት መንግስታት በበርካታ ጉዳዮች ላይ በጋራ እንደሚሰሩ ጠቁመዋል።
የግብርና እና የገጠር ልማት ስራዎች ለዚህ ተጠቃሽ መሆናቸውን ጠቁመው፤ በሀገራቱ መካከል ትልቅ ትብብር እና መተማመን መኖሩን ተናግረዋል።