የጥናትና ምርምር ሥራዎች እውቅና ያላቸውና ዘመን ተሻጋሪ ለማድረግ ትኩረት ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
የጥናትና ምርምር ሥራዎች እውቅና ያላቸውና ዘመን ተሻጋሪ ለማድረግ ትኩረት ተደርጓል
           አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 22/2018(ኢዜአ)፡-የጥናትና ምርምር ሥራዎች እውቅና ያላቸውና ዘመን ተሻጋሪ እንዲሆኑ የባለሙያዎችን አቅም ለማጎልበት በከፍተኛ ትኩረት እየሰራ መሆኑን የኦሮሞ ጥናትና ምርምር ኢንስትቲዩት ገለጸ።
የኦሮሞ ጥናትና ምርምር ኢንስቲትዩት የተለያዩ ጥናትና ምርምር ለሚያከናወኑ ባለሙያዎች ሳይንሳዊ ዕውቀት የሚያስጨብጥ የአቅም ግንባታ ስልጠና እየሰጠ ነው፡፡
                
                
  
የኦሮሚያ ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ሃላፊ ረዳት ፕሮፌሰር ደራራ ከተማ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ስልጠናው የክልሉን እምቅ አቅም ለሀገር ውስጥና በውጭ ዓለማት ለማስተዋወቅ ያለመ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የቋንቋ ልማት አንዱ የባህል ህዳሴ መሆኑን በማንሳት፤ ቋንቋው በአስተዳደር፣ በትምህርት፣ በመገናኛ ብዙኃንና በምጣኔ ሀብት ዘርፎች ጥቅም ላይ እንዲውል ይደረጋል ብለዋል፡፡
የገዳ ሥርዓት በክልሉ የማኅበራዊ መስተጋብር ውስጥ ያለውን ሚና ማጎልበት፣ የሕዝቡን ትክክለኛ ታሪክ በምርምር፣ በትምህርትና በሥነ ጽሁፍ ለማስተዋወቅ ያለመ መሆኑንም አንስተዋል፡፡
የኦሮሞ ጥናትና ምርምር ኢንስቲትዩት ምክትል ዳይሬክተር ዝናቡ አስራት ተቋሙ የሕዝብን ታሪክ፣ ቋንቋ፣ ባህልና ዕውቀት መሰረት ያደረጉ ጥናቶች በማከናወን የባህል ሕዳሴን ለመደገፍ መቋቋሙን ገልጸዋል፡፡
ኢንስቲትዩቱ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በመቀናጀት እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ ተመራማሪዎች ለምርምር ሥራ የሚያስፈልጋቸውን ሙያዊ ክህሎት መገንባት ያስችላል ብለዋል፡፡
የምርምር ሥራዎች የሕዝቡን ህይወት በሚያሻሽሉ በጤና፣ በትምህርት፣ በኢኮኖሚና ሌሎች መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩሩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
የሕዝቡ ቋንቋ እና ታሪክ በሳይንሳዊ መንገድ በማጥናት ለክልሉ ባህል ዕድገትና ልማት መሰረት የሚጥል ተቋም መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ይህም ለክልሉ ባህል ዕድገትና ለልማት ሥራዎች መሠረት የሚጥል ተቋም መሆኑን በማንሳት፤ የወል ትርክትን የሚገነቡ ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የማህበረሰቡን ችግር ፈቺና ዘመን ተሻጋሪ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን ለማከናወን የተመራማሪዎችን አቅም መንገባት እንደሚገባ ገልጸው፤ ኢንስቲትዩቱ በትኩረት እየሰራበት ነው ብለዋል፡፡
ኢንስቲትዩቱ በ73 ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ የተለያዩ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን እየሰራ መሆኑም ተገልጿል።