ኢንዱስትሪው በተኪ ምርት እና ወጪ ንግድ የሚያስመዘግባቸው ስኬቶች ለጥቅል ሀገራዊ ዕድገት ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢንዱስትሪው በተኪ ምርት እና ወጪ ንግድ የሚያስመዘግባቸው ስኬቶች ለጥቅል ሀገራዊ ዕድገት ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 22/2018(ኢዜአ)፦ ኢንዱስትሪው በተኪ ምርት እና ወጪ ንግድ የሚያስመዘግባቸው ስኬቶች ለጥቅል ሀገራዊ ዕድገት ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ሎሚ በዶ ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን ሁለተኛ መደበኛ ስብሰባ ከምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ በ2017 በጀት ዓመት ኢንዱስትሪው 13 በመቶ በማስመዝገብ ለሀገር ውስጥ ጠቅላላ ምርት ዕድገት 3 ነጥብ 7 በመቶ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ገልጸዋል፡፡
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ሎሚ በዶ ለኢዜአ እንዳሉት፤ መንግስት ብዝሃ ኢኮኖሚን በማስፋት ብልጽግናን ለማረጋገጥ በትኩረት እየሰራ ነው፡፡
ከኢኮኖሚው ብዝሃ ዘርፎች መካከል ኢንዱስትሪው አንደኛው መሆኑን አንስተው፤ ዘርፉ በተኪ ምርትና ወጪ ንግድ ላይ አበረታች ውጤት ማስመዝገቡን ገልጸዋል፡፡
ኢንዱስትሪው በጥቅል ሀገራዊ ዕድገት ላይ የጎላ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው ያሉት ምክትል አፈ ጉባኤዋ፤ ኢትዮጵያ በራሷ አቅም ለማደግ የሰነቀችውን ራዕይ ለማሳካት ያግዛል ብለዋል፡፡
ይህም ኢትዮጵያ የጀመረችውን የብልፅግና ጉዞ ለማረጋገጥ በምታደርገው ጥረት የሚገድባት ምንም ነገር እንደሌለ ማሳያ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ የማደግ፣ የመለወጥና የማንሰራራት ጉዞ በትክክለኛ መንገድ ላይ መሆኑን የገለጹት ምክትል አፈ ጉባኤ ሎሚ፤ በዘርፉ የሚወጡ ፖሊሲዎች፣ ዕቅዶችና ህጎች ኢንዱስትሪውን የሚያሻግሩ ናቸው ብለዋል፡፡
መንግስት የዘርፉን ተወዳዳሪነት ለማሳደግ ከብድር አቅርቦት ጀምሮ በርካታ ማበረታቻዎችን እየሰጠ መሆኑንም ተናግረዋል።
በኢንዱስትሪው ዘርፍ በቁርጠኝነት የተከናወኑ ስራዎች ውጤት እየተመዘገበባቸው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡