ቀጥታ፡

በውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት ለ800 ሺህ ዜጎች የስራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዷል - ሚኒስቴሩ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 22/2018 (ኢዜአ)፡- በ2018 በጀት ዓመት በውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት ለ800 ሺህ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር አቅዶ እየሠራ መሆኑን የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር አስታወቀ።

የዜጎችን ክብር፣ መብት፣ ደኅንነትና ተጠቃሚነትን በሚያረጋግጥ መልኩ የውጭ ሀገራት የሥራ ስምሪት ላይ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን በሚኒስቴሩ የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ አበበ ዓለሙ ለኢዜአ ገልጸዋል።

የውጭ ሀገራት የሥራ ስምሪት በየጊዜው እያደገ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከ2014 ዓ.ም በፊት ከነበረበት 40ሺህ ገደማ በ2017 ዓ.ም 503 ሺህ እንዲሁም በ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ከ136ሺህ በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አብራርተዋል።

የውጭ ሀገራት የሥራ ስምሪቱን ለማሳካት በሚደረጉ ሂደቶች የነበሩ እንግልቶችንና ወጪዎችን ማስቀረት የቻለ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ዘመናዊ አሠራር መዘርጋቱንም አስታውቀዋል።

በሌላ በኩል በሥራ ስምሪት መዳረሻ ሀገራት ያሉ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች አማካኝነት የዜጎችን መብት፣ ደኅንነትና ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የሚያስችል ሥርዓት መዘርጋቱን ተናግረዋል።

እስካሁን ከኩዌት፣ ሊባኖስ፣ ሳዑዲ ዓረቢያ፣ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች፣ ዮርዳኖስና ኳታር ጋር የመግባቢያ ስምምነት ተፈርሞ ወደ ተግባር መገባቱንና በቀጣይም የመዳረሻ ሀገራትን ለማስፋት እየተሠራ ነው ብለዋል።

የሙያ ዓይነቶችን ለማብዛት በቀጣይ በስፋት የሚታሰቡ ዘርፎች እንደሚኖሩ ጠቁመው፤ አሁን ላይ ተግባራዊ እየተደረጉ ያሉት የቤት ረዳትነት፣ ቤት አያያዝ፣ የቤተሰብ እንክብካቤ፣ ሾፌር፣ ሴኩሪቲ ናቸው መሆናቸውን ገልጸዋል።

የሰለጠነ እና በከፊል የሰለጠነ የሰው ኃይል የሥራ ስምሪት በቀጣይ እንዲኖር እየታሰበበት መሆኑንም ጨምረው ተናግረዋል።

የመዳረሻ ሀገራትን ለማስፋት እየተደረገ ባለው ጥረት ከሰሞኑ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ከጣልያን መንግሥት ጋር የተፈራረሙት ወደ አውሮፓ ገበያ ለመግባት ትልቅ ዕድል የሚፈጥር መሆኑን ጠቅሰዋል።

ጣልያን ከኢትዮጵያ የሰለጠነና በከፊል የሰለጠነ የሰው ኃይል ለመቀበል ዝግጁ መሆኗ መገለጹንም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም