የኢትዮጵያ አየር መንገድ አፍሪካን ከዓለም ጋር የማስተሳሰር አገልግሎቱን አጠናክሮ ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ አፍሪካን ከዓለም ጋር የማስተሳሰር አገልግሎቱን አጠናክሮ ይቀጥላል
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 22/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አፍሪካን ከመላው ዓለም ጋር በማስተሳሰር የላቀ አገልግሎት መስጠቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው ገለጹ።
ዋና ሥራ አስፈጻሚው ለአፍሪካ የአየር ትራንስፖርት እድገትና ትስስር ላበረከቱት የላቀ አስተዋጽኦ ከጂ.ኢ ኤሮስፔስ ኩባንያ ሽልማት ተበረከተላቸው።
በመረሃ-ግብሩ ላይ በኢትዮጵያ የአሜሪካን አምባሳደር ኢርቫን ማሲንጋ፣ የጂ.ኢ ኤሮስፔስ ኩባንያ የኮሜርሻል እና ኢንጅን አገልግሎት ዘርፍ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሩሴል ስቶክስ፣ የአየር መንገዱ ከፍተኛ አመረራር አባላትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
የጂ.ኢ ኤሮስፔስ ኩባንያ የኮሜርሻል እና ኢንጅን አገልግሎት ዘርፍ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሩሴል ስቶክስ በዚሁ ወቅት፤ የአየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው የተቋሙን ስኬት እና ስትራቴጂካዊ ዕድገት በማስቀጠል ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን አንስተዋል።
በተጨማሪም የአፍሪካ የአየር ትራንስፖርት እድገትና ትስስር እንዲፋጠን ላሳዩት ቁርጠኛ አመራር ሰጭነት ጭምር ሽልማቱ የተበረከተላቸው መሆኑንም ገልጸዋል።
ከጂ.ኢ ኤሮስፔስ ኩባንያ ጋር በአጋርነት ለአየር መንገዱ የላቀ እድገትና ጥራት ያለው አገልግሎት በቅርበት እንዲሰራ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን አንስተዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው በበኩላቸው፣ የጂ.ኢ ኤሮስፔስ ኩባንያ ላበረከተላቸው እውቅና ምስጋና አቅርበዋል።
በቀጣይም የኢትዮጵያ አየር መንገድ አፍሪካን ከመላው ዓለም ጋር በማስተሳሰር የላቀ አገልግሎት መስጠቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል በማስታወስ፣ ሽልማቱ የግሌ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ አየር መንገድ መላው ሰራተኞች ድምር የስራ ጥረት ውጤት ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድን ስኬትና ዕድገት ማስቀጠል የቻሉት የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው በቅርቡ የ2025 የአፍሪካ ኢምፓክት አዋርድ በአሜሪካን እንዲሁም “Leadership in Connecting Africa through Transport Award” በአክራ ጋና ተሸላሚ መሆናቸው ይታወሳል።
የስታር አሊያንስ አባል የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ከ66 በላይ የአፍሪካ ከተሞች ላይ የሚበር ሲሆን፤ በየዓመቱ አፍሪካን ከመላው ዓለም በማገናኘት በርካታ ሽልማቶችን አሸናፊ ነው።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በስካይትራክስ ለስምንተኛ ጊዜ የአፍሪካ ምርጡ አየር መንገድ የተባለ ሲሆን፤ የአፍሪካ ምርጥ የቢዝነስ ክፍል፣ የአፍሪካ ምርጥ የኢኮኖሚ ክፍል እና በአፍሪካ ቢዝነስ ክፍል ምርጥ ምግብ አገልግሎት ሰጪ አየር መንገድ በመባል የ2025 ሽልማቶችን ማሸነፍ ችሏል፡፡
አየር መንገዱ አስተማማኝ የአየር ትራንስፖርት በመስጠት የሀገሪቷን ኢኮኖሚና፤ ቱሪዝም ለማሳደግ እንዲሁም ኢትዮጵያን የኮንፈረንስ እና የንግድ ማዕከል በማድረግ የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ለማሳደግ ተግቶ እየሰራ ይገኛል፡፡