ኢትዮጵያ ታሪካዊ እና ዓለም አቀፋዊ ህጎችን ተከትላ በሰላማዊ መንገድ ወደ ቀይ ባህር እንድትመለስ እንሰራለን - የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ታሪካዊ እና ዓለም አቀፋዊ ህጎችን ተከትላ በሰላማዊ መንገድ ወደ ቀይ ባህር እንድትመለስ እንሰራለን - የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 21/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ታሪካዊ እና ዓለም አቀፋዊ ህጎችን ተከትላ በሰላማዊ መንገድ ዳግም ወደ ቀይ ባህር እንድትመለስ አበክረን እንሰራለን ሲሉ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ገለጹ፡፡
በዓለም ላይ ከባህር በር በ60 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ሆና ወደብ የሌላት ሀገር ኢትዮጵያ ብቻ መሆኗን በመግለጽ፤ ምክር ቤቱ ታሪካዊና ህጋዊ ጥያቄዋ ምላሽ እንዲያገኝ ሚናውን እንደሚወጣ ነው የገለፁት።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን ሁለተኛ መደበኛ ስብሰባ ከምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ እንደገለጹት፤ የቀይ ባህር ጉዳይ ሕጋዊ፣ ታሪካዊ፣ መልክዓ ምድራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄ ነው፡፡
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውሃ፣ መስኖ፣ ቆላማ አካባቢዎችና የአካባቢ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አወቀ አምዛዬ (ዶ/ር) ለኢዜአ በሰጡት ማብራሪያ፤ ቀይ ባህር ኢትዮጵያ ፍትሕ ያጣችበት አጋጣሚ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በምክር ቤቱ የፕላን፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ደሳለኝ ወዳጄ የባህር በር የኢትዮጵያ ህዝብ የተቀማ ሀብቱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ሳትፈለግ ያጣችውን የባህር በር በድርድርና በሰላማዊ መንገድ እንዲመለስላት ፍትሐዊ ጥያቄ አቅርባለች ቀና ምላሽ ይገባታል ብለዋል፡፡
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አማካሪ ኮሚቴ አባል አብርሃም በርታ (ዶ/ር) በዓለም ላይ ከባህር በር በ60 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ሆና ወደብ የሌላት ሀገር ኢትዮጵያ ብቻ መሆኗን ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም ኢትዮጵያ ታሪካዊ እና ዓለም አቀፋዊ ህጎችን ተከትላ በሰላማዊ መንገድ ዳግም ወደ ቀይ ባህር መመለስ ይገባታል ብለዋል፡፡
በምክር ቤቱ የፕላን፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ደሳለኝ ወዳጄ በበኩላቸው፤ ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ መነሻ በማድረግ የውጭ ግንኙነቶችን እንደሚወስን ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም ህጋዊና ታሪካዊ ጥያቄዎች ተገቢ ምላሽ እንዲያገኙ አስፈላጊ አዋጆችን በማጽደቅ፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ድምጽ በማሰማትና የጋራ ውሳኔ በማስተላለፈ ለተፈጻሚነቱ አበክሮ ይሰራል ብለዋል፡፡