ኢትዮጵያ የምታዘጋጀው የሴካፋ ዞን ከ17 ዓመት በታች አፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የምድብ ድልድል ይፋ ሆነ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የምታዘጋጀው የሴካፋ ዞን ከ17 ዓመት በታች አፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የምድብ ድልድል ይፋ ሆነ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 21/2018 (ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ የምታዘጋጀው የሴካፋ ዞን ከ17 ዓመት በታች አፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የምድብ ድልድል ዛሬ ይፋ ሆኗል።
16ኛው ከ17 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ እ.አ.አ በ2026 በሞሮኮ አስተናጋጅነት ይከናወናል።
በውድድሩ ላይ የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ የእግር ኳስ ማህበራት ምክር ቤት(ሴካፋ) ዞንን ወክለው የሚሳተፉ ሁለት ሀገራት የሚለዩበት የማጣሪያ ውድድር በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት ከህዳር 6 እስከ 23 ቀን 2018 ዓ.ም ይካሄዳል።
ሴካፋ የማጣሪያ ውድድሩ የምድብ ድልድል ዛሬ በዩጋንዳ ይፋ አደርጓል።
በምድብ አንድ አዘጋጇ ኢትዮጵያ ከሶማሊያ፣ ኬንያ፣ ደቡብ ሱዳን እና ሩዋንዳ ጋር መደልደሏን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።
ዩጋንዳ፣ ታንዛንያ፣ ጅቡቲ፣ ሱዳን እና ብሩንዲ በምድብ ሁለት የተደለደሉ ሀገራት ናቸው።
ውድድሩ በአበበ ቢቂላ እና ድሬዳዋ ኢንተርናሽናል ስታዲየሞች ይካሄዳል።
በማጣሪያው ለፍጻሜ የሚያልፉት ሁለት ሀገራት የሴካፋ ዞንን ወክለው ለአፍሪካ ዋንጫ ያልፋሉ።
እ.አ.አ በ2026 በሚካሄደው 16ኛው ከ17 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ አዘጋጇ ሞሮኮን ጨምሮ 16 ሀገራት ይሳተፋሉ።