ቀጥታ፡

 የአፍሪካ የብዝሃ ህይወት ቃል ኪዳን እና የኢትዮጵያ አረንጓዴ ጉዞ 

ብዝኃ ህይወት ሁሉንም ሥነ-ሕይወታዊ ኃብቶች፣ እፅዋት፣ እንስሳትና ደቂቅ አካላት እንዲሁም በውስጣቸው የያዟቸው ዘረ-መሎችና እነዚህ የሚፈጥሯቸውን ውህዶች የሚያካትት ነው። የሁሉም ስርዓተ ምህዳር እና የሰው ልጆች የመኖር መሰረት ነው ብዝሃ ህይወት። 
 
እንደ አንዳንድ ጥናቶች ከሆነ በዓለማችን ካሉ ህይወት ካላቸው 8 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዝርያዎች መካከል 80 በመቶዎቹ ገና ያልተገኙ ናቸው። የዓለም ብዝሃ ህይወት ቁልፍ ጠቀሜታዎች አሉት። የምግብ ምርታማነት፣ ንጹህ ውሃ እና አየር፣ ለርክበብናኝ (ፖሊኔሽን) እና አየር ንብረትን መቆጣጠርን ጨምሮ በርካታ ጠቃሜታዎች እንዳሉት የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ።
 
ብዝሃ ህይወት ከ44 ትሪዮን ዶላር በላይ ወይም የዓለምን ዓመታዊ 50 በመቶ ጥቅል ምርት (ጂዲፒ) ይሸፍናል። 



 
የዓለም የብዝሃ ህይወት እና የስነ ምህዳር አገልግሎቶች የበይነ መንግስታት የሳይንስ ፖሊሲ መድረክ ((IPBES) በሚቀጥሉት 10 ዓመታት ውስጥ በሰው የተለያዩ ተግባራት፣ የአየር ንብረት ለውጥ እና የመሬት አጠቃቀም ምክንያት አንድ ሚሊዮን ገደማ ህይወት ያላቸው ዝርያዎች ሊጠፉ እንደሚችሉ ስጋቱን አስቀምጧል።
 
በዚህ የዓለም ቀውስ ውስጥ አፍሪካ የብዝሃ ህይወት እምቅ ሀብቶች ያላት አህጉር ሆና ተገኝታለች። የብዝሃ ህይወቱ በርካታ እና ጫና መቋቋም የሚችሉ የአይበገሬነት አቅም ያላቸው ናቸው። የዓለም አንድ አምስተኛ እጽዋት፣ አጥቢ እንስሳት እና  አዕዋፋት የሚገኙት በአፍሪካ ነው። 
 
ከ50 ሺህ በላይ የእጽዋት ዝርያዎች፣ 1 ሺህ 100 አጥቢ እንስሳት፣ 2 ሺህ 500 የአዕዋፋት እና ከ3000 በላይ የአሳ ዝርያዎች ይገኛሉ። 
 
የዓለማችን ሁለተኛው ጥብቅ ደን የኮንጎ ጥቅጥቅ ደን፣ የቦትስዋና ኦካንጋቮ ዴልታ፣ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ስፍራዎች እና የማዳጋስካር ልዩ ስነ ምህዳሮችና ዝርያዎች ከአፍሪካ ዋነኛ ብዝሃ ህይወቶች መካከል ይጠቀሳሉ። የአፍሪካ ብዝሃ የኔዜጎችን የአኗኗር ዘይቤ ከማሻሻል ባለፈ የአፍሪካን የኢኮኖሚ እድገት በዘላቂነት ማስቀጠል የሚችል አቅም ያለው ነው።
 
ይሁንና የአፍሪካ ብዝሃ ህይወቶች ለተለያዩ ፈተናዎች የተጋለጡ ናቸው። አህጉሪቷ በየዓመቱ 3 ነጥብ 9 ሚሊዮን ሄክታር ገደማ ደን እንደምታጣ መረጃዎች ያሳያሉ። እ.አ.አ በ2050 2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ህዝብ ይደርሳል ተብሎ የሚጠበቀው የአፍሪካ ህዝብ፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ ህገ ወጥ አደን ፣ ዘላቂነት የጎደለው የመሬት አጠቃቀም እና ብክለት የአህጉሪቷን ብዝሃ ህይወት ስርዓት እየጎዱ ይገኛሉ።



 
የአፍሪካ ጥብቅ ስፍራዎች ለማስተዳደር በዓመት ከ10 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚያስፈልግ ቢሆንም አንዳንድ ሀገራት በቂ ኢንቨስመንት እየመደቡ አይገኝም።
 
አፍሪካ የሶስትዮሽ ተፈጥሯዊ ቀውሶችን እያስተናጋደች ትገኛለች ማለት ይችላል። የብዝሃ ህይወት መመናመን፣ ብክለት እና የአየር ንብረት ለውጥ ከፍተኛ ተግዳሮቶች ናቸው። የአስተዳደር ስርዓት አለመጠናከር፣ የተገደበ የፋይናንስ አቅርቦት እና የአካባቢ ማህበረሰብ መሪዎች በውሳኔ መስጠት ውስጥ አለመሳተፋቸው በዋናነት የሚጠቀሱ ፈተናዎች እንደሆኑም ይነገራል።
 
የአፍሪካ ሀገራት የብዝሃ ህይወት ችግሮችን ለመፍታት የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰዱ ይገኛል። ከነዚህም አንዷ ኢትዮጵያ ናት። ኢትዮጵያም ከፍተኛ የብዝኃ ሕይወት ኃብት ካላቸው አገራት መካከል አንዷ ናት።

አሁን ላይ አገሪቱ ከ6 ሺህ በላይ የእፅዋት ኃብቶች ያላት ሲሆን፤ ከእነዚህም ውስጥ 600 ወይም 10 በመቶ የሚሆኑት በአገሪቱ ብቻ የሚገኙ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ብዝኃ ሕይወት ኢንስቲትዩት መረጃ ያመለክታል። 


 

ጎን ለጎንም የወፍ ዝርያዎችን ጨምሮ በየብስና በውኃ አካላት ውስጥ የሚኖሩ የተለያዩ ዓይነት ዝርያ ያላቸው በርካታ እንስሳት በኢትዮጵያ ይገኛሉ።

ይሁንና የየብስና የውኃማ አካላት አካባቢ መለወጥ ለእነዚህ ብዝኃ ሕይወት ኃብቶች ሥጋት እየሆነ መምጣቱን ነው ኢንስቲትዩቱ የገለጸው። 

በኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ፣ ብክለትና ዘለቄታዊ ያልሆነ የተፈጥሮ ኃብት አጠቃቀም ለብዝኃ ሕይወት ኃብቶች መመናመን ምክንያቶች ናቸው። 

የሕዝብ ቁጥር መጨመርን ተከትሎ ደን ወደ እርሻ መሬትነት መቀየር እንዲሁም መጤ ወራሪ አረሞች ነባር አገር በቀል ዝርያዎች የሚበቅሉበትን ሥፍራ መያዝም ሌላኛው ምክንያት ነው። 

ይህንንም ተከትሎ ወይራ፣ ዝግባ፣ ቀረሮ፣ ዋንዛ፣ ጥቁር እንጨትና ኮሶ እየተመናመኑ ካሉ የእፅዋት ብዝኃ ሕይወት ዝርያዎች መካከል ይጠቀሳሉ። 

ዝርያዎቹ አንዴ ከጠፉ መልሰው የማይገኙ በመሆናቸው ኢንስቲትዩቱ ዝርያዎቹን የማራባትና የማብዛት ሥራ በልዩ ትኩረት እያከናወነ እንደሚገኝ አመልክቷል። 

ከእነዚህም በተጨማሪ የኢኮኖሚ ጠቀሜታ ያላቸውና በኢትዮጵያ ብቻ ያሉ የእፅዋትና እንስሳት ብዝኃ ሕይወት ዝርያዎችን የመጠበቅ ሥራ እየተከናወነ ነው። 

በዚህም የቀረሮ የእጽዋት ዝርያ የማብዛት ሥራ እንዲሁም በተለያዩ አካባቢዎች የተመናመኑ የዳልጋ ከብቶች ወደ ነበሩበት የመመለስ ሥራም በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል።  

በተመሳሳይ "የሸኮ ዳልጋ ከብት" እየተባለ የሚጠራውን ዝርያ የማብዛት እንዲሁም በጣና ኃይቅ የዓሳ ዝርያዎች ላይ ያለውን መመናመን ለመቀልበስም የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም ነው ኢኒስቲትዩቱ ያስታወቀው።  

ጥብቅ አካባቢዎችን የማስፋት፣ የእፅዋት አፀድ ጥበቃ፣ የዘረመልና የማኅበረሰብ የዘር ባንኮችን በየአካባቢው የማስፋት ተግባርም እየተሰራ መሆኑን አመልክቷል።



  
የአረንጓዴ አሻራ መርኃ-ግብርም የብዝኃ ሕይወትን ከመጠበቅና ከማስቀጠል አኳያ ትልቅ አስተዋጽዖ እያበረከተ መሆኑን አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ ያሏትን የብዝኃ ሕይወት ሃብቶች የመጠበቅ ተልዕኮ የተሰጠው የኢትዮጵያ ብዝሃ ሕይወት ኢንስቲትዩትም ኃብቶቹን የማንበር (የመጠበቅ)፣ ዘለቄታዊ አጠቃቀምና ፍትሃዊ የጥቅም ተጋሪነት ላይ እየሰራ ይገኛል።

በአፍሪካ ብዝሃ ህይወት ሀብቶች፣ እድሎች፣ ፈተናዎች እና ቀጣይ እርምጃዎች የሚመክር ጉባኤ በቦትስዋና ጋቦሮኒ ከጥቅምት 23 እስከ 26 ቀን 2018 ዓ.ም ይካሄዳል።  

“የብዝሃ ህይወትን በዘላቂነት በመጠቀም የአፍሪካን ብልጽግና ማረጋገጥ” የጉባኤው መሪ ቃል ነው። 

ጉባኤው ለአፍሪካ ብዝሃ ህይወት መመናመን፣ የአየር ንብረት ለውጥ እና ብክለት የተቀናጀ አህጉራዊ ምላሽ መስጠት የሚያስችል መድረክ መሆኑን የአፍሪካ ህብረት መረጃ ያመለክታል።

የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች፣ የአካባቢ ጥበቃ ሚኒስትሮች፣ የዓለም የብዝሃ ህይወት ጥበቃ መሪዎች እና ተመራማሪዎች፣ ሀገር በቀል የማህበረሰብ መሪዎች፣ ባለሀብቶች፣ የግሉ ዘርፍ ተዋንያን፣ የሲቪክ ማህበረሰብ ተቋማት፣ ዓለም አቀፍ አጋሮች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ይሳተፋሉ።
 
የአፍሪካ ቀዳሚ የብዝሃ ህይወት አጀንዳዎች  ምክክር ይደረግባቸዋል። አህጉር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ ትስስርን ማጠናከር እና ለብዝሃ ህይወት ክብካቤ የፋይናንስ ሀብትን በተቀናጀ ሁኔታ ማሰባሰብ ሌሎች የጉባኤው አጀንዳዎች ናቸው። 

ኢትዮጵያ እና የጉባኤው አዘጋጅ ቦትስዋን ጨምሮ የአፍሪካ ሀገራት በብዝሃ ህይወት ጥበቃ እያከናወኗቸው ያሉ ስራዎችን አስመልክቶ ልምዳቸውን ያጋራሉ።

እ.አ.አ በ2026 በአርሜኒያ በሚካሄደው 17ኛው የዓለም የብዝሃ ህይወት ጉባኤ (ኮፕ 17) ጨምሮ በሌሎች ዓለም አቀፍ መድረኮች የአፍሪካን ድምጽ በጋራ ማሰማት በሚቻልበት ሁኔታ ላይም ምክክር ይደረጋል።

ጉባኤው አንድ ብዝሃ ህይወት የልማት አቅም ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ ብልጽግና አረጋጋጭ ሞተር መሆኑ ግልጽ መልዕክት የሚተላለፍበት መድረክ ነው። ፍላጎቶች ተጨባጭ እና መሬት ወደወረዱ መፍትሄዎች ማውረጃ አማራጭ ሆኖም ያገለግላል።
 
በአርሜኒያ ለሚገሄደው ዓለም አቀፍ ጉባኤ አፍሪካ ፍትሃዊ የፋይናንስ አቅርቦት እንድታገኝ፣ ሁሉን አቀፍ የብዝሃ ህይወት አስተዳደር እንዲረጋገጥ እና ለፍትሃዊ የጥቅም ተጋሪነት ድምጿን ለማሰማት ስንቅ ለሚሆን የሚያስችል አህጉራዊ መድረክ ጭምር ነው ማለት ይቻላል።

በአፍሪካ ያለውን የብዝሃ ህይወት አቅም በውጤታማ የአስተዳደር ስርዓት፣ አካታች የማህበረሰብ ተሳትፎ እና ዓለም አቀፍ ትብብር አማካኝነት ወደ ዘላቂ እድገት ምንጭነት ማሸጋገር እንደሚቻል ጥርጥር የለውም።

የአፍሪካ የብዝሃ ህይወት ጥበቃ ስራ ለዓለም የብዝሃ ህይወት ግቦች መሳካት ትልቅ አበርክቶ ይኖረዋል። 

በብዝሃ ህይወት ላይ መዋዕለ ንዋይን ማፍሰስ ለአፍሪካ መጻኢ ጊዜ መሰረት እንደመጣል ይቆጠራል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም