የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶች ለወጣቶች ሰፊ የስራ ዕድልን በመፍጠር ተጠቃሚነታችንን የሚያሳድጉ ናቸው- ወጣቶች - ኢዜአ አማርኛ
የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶች ለወጣቶች ሰፊ የስራ ዕድልን በመፍጠር ተጠቃሚነታችንን የሚያሳድጉ ናቸው- ወጣቶች
 
           ጎንደር/ ገንዳ ውሃ፤ ጥቅምት 21/2018 (ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ የወጠነቻቸው የልማት ፕሮጀክቶች ለወጣቶች ሰፊ የስራ ዕድልን በመፍጠር ተጠቃሚነታችንን የሚያሳድጉ ናቸው ሲሉ የጎንደርና ገንዳ ውሃ ከተሞች ወጣቶች ገለጹ።
የጎንደርና የገንዳ ውሃ ከተሞች ወጣቶች በወቅታዊ ጉዳይ ዙሪያ የምክክር መድረክ አካሄደዋል፡፡
በጎንደር ከተማ በተካሄደው መድረክ የተሳተፈው ወጣት ደሴ ማለደ እንደገለጸው በአገራችን ሊካሄዱ የታቀዱ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ወጣቶች በሀገራቸው ሰርተው እንዲለወጡ የሚጨበጥ ተስፋን የሚሰጡ ናቸው።፡
በቅርቡ ይፋ የተደረጉት የጋዝ ማምረቻና የነዳጅ ማጣሪያ፣ የማዳበሪያ ፋብሪካ፣ የአውሮፕላን ማረፊያና ሌሎች ፕሮጀክቶች ለወጣቱ ሰፊ የስራ ዕድልን በማመቻቸት ለፕሮጀክቶቹ ስኬት የተለየ አበርክቶ እንዲኖረው ያደርጋሉ ብሏል።
                
                
  
የገንዳ ውሃ ከተማ ነዋሪው ወጣት ጀማል መሃመድ በበኩሉ በሀገራችን የተጀመሩ ሜጋ ፕሮጀክቶች እንዲሳኩ እኛ ወጣቶች ሰላማችንን በመጠበቅና አንድነታችንን በማጠናከር በህብረት እንሰራለን ሲል ተናግሯል።
መንግስት ለግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች የሰጠው ትኩረት ወጣቱ ሰፊ የስራ እድል አንዲያገኝ ምቹ መደላድልን የሚፈጥር በመሆኑ የአካባቢያችንን ሰላም በማዝለቅ ፕሮጀክቶቹ እውን እንዲሆኑ እንሰራለን ብሏል።
የሰላምና ልማት መረጋገጥ በቀጥታ የወጣቱን ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው ያለው ደግሞ ሌላው የከተማው ወጣት አስማረ ማለደ ነው።
በዚህም መንግስት ሰላምና ልማትን በማረጋገጥ የአገራችን እድገት ለማፋጠን በሚያደርገው ጥረት በንቃት በመሳተፍ የራሱንና የሌሎች ወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማስፋት እንደሚሰራም ተናግሯል።
ወጣት ኤርሚያስ አቡሃይ በበኩሉ "እኛ ወጣቶች የሀገራችንን እድገትና ብልፅግና በማረጋገጥ ያለንን ህልምና ተስፋ ለማሳካት መስራት ይጠበቅብናል ብሏል፡፡
ሌላኛዋ የመድረኩ ተሳታፊ ወጣት ሙሉ ተገኘ በበኩሏ ፅንፈኝነትን በማውገዝና በመታገል በአካባቢው የተጀመሩ የልማትና የህግ ማስከበር ተግባራት እንዲሳኩ ኃላፊነቷን እንደምትወጣም ገልፃለች።
                
                
  
የጎንደር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ተወካይ አቶ ነጻነት መንግስቴ እንደገለጹት የኢትዮጵያን ማደግና መለወጥ የማይሹ የውስጥና የውጪ ሃይሎች የሚፈጥሩትን ሴራ በማክሸፍ ወጣቱ ታሪካዊ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል ብለዋል፡፡
የተጀመሩ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ለወጣቱ ሰፊ የስራ እድል በመፍጠር ተጠቃሚነቱን የሚያረጋግጡ መሆናቸውን ጠቁመው ለስኬታቸው የጋራ ርብርብ ይጠይቃል ብለዋል።
የገንዳውሃ ከተማ አስተዳደር ወጣቶች፣ ባህልና ስፖርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኪሩቤል መንግስቴ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ እያስመዘገበች ያለውን አንፀባራቂ የልማት ድሎችን ለማስቀጠል የወጣቶች ተሳትፎ ወሳኝ ነው።
ሀገራችንን ቀዳሚ እንድትሆን ለሚያደርጉ ሜጋ ፕሮጀክቶች መሳካት ወጣቱ ትውልድ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት እንዲወጣም አሳስበዋል።
በተካሄዱት የውይይት መድረኮች ላይም የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ ወጣቶችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።