በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተከናወኑ ያሉ አበረታች የልማት ተግባራት እንዲጠናከሩ የድርሻችንን እንወጣለን -የተለያዩ ከተሞች ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተከናወኑ ያሉ አበረታች የልማት ተግባራት እንዲጠናከሩ የድርሻችንን እንወጣለን -የተለያዩ ከተሞች ነዋሪዎች
 
           ወላይታ ሶዶ/ሀዋሳ/ጂንካ፤ ጥቅምት 21/2018 (ኢዜአ):- በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተከናወኑ ያሉ አበረታች የልማትና የሰላም ማስከበር ተግባራት እንዲጠናከሩ የድርሻቸውን እንደሚወጡ በወላይታ ሶዶ፣ ሀዋሳና ጂንካ ከተሞች ነዋሪዎች ተናገሩ።
በሀገሪቱ ወቅታዊ የልማትና ሰላም ግንባታ ዙሪያ ኢዜአ በየከተሞቹ ነዋሪዎችን አነጋግራል።
የወላይታ ሶዶ ከተማ ነዋሪ አቶ ነጋ አንጎሬ፤ እንደ ሀገር እየተካሄዱ ያሉ የልማትና የሰላም ግንባታ ስራዎች አበረታች መሆናቸውን ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም ተጀምረው የማይጠናቀቁ የልማት ስራዎች የመልካም አስተዳደር ችግር ሆነው የቆዩትን ከለውጡ ወዲህ በመሻሻል መሰረታዊ ለውጥ ማምጣት መቻሉን አንሰተዋል።
ይህም ነባር ፕሮጀክቶችን ከማጠናቀቅ ጎን ለጎን በአዲስ አስተሳሰብ የሚጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶች በጥራትና በፍጥነት እየተጠናቀቁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
እንደ ሀገር አሁን ላይ በሰላም ግንባታና በልማት መስክ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ለትውልድ የሚተላለፉ በመሆናቸው ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የበኩላቸውን እንደሚውጡ ተናግረዋል።
በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞችም ሆነ ገጠር አካባቢዎች እየታየ ያለው የልማት እንቅስቃሴ የተሻለች ኢትዮጵያን እንድናይ መሰረት እየጣለ ነው ያሉት ደግሞ ሌላው የወላይታ ሶዶ ከተማ ነዋሪ አቶ ከበደ ኤሌ ናቸው።
ለዚህም የኮርደር ልማት፣ የወንዝ ዳር ልማትና አረንጓዴ አሻራን ለአብነት ጠቅሰዋል።
ሰላም ለሁሉም ነገር መሰረት ነው ያሉት አቶ ከበደ፤ መንግስት በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም ሰፍኖ ልማት እንዲፋጠን እያከናወናቸው ያሉት ውጤታማ ተግባራት የሚያኮሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ከሀዋሳ ከተማ ነዋሪዎች መካከል ተካልኝ አባ እንዳሉት፤ መንግስት ለሰላም ግንባታና ለልማት በሰጠው ትኩረት ተጨባጭ ለውጥ እየመጣ ነው።
በከተሞች እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት የከተሞችን ብቻ ሳይሆን የሀገር ገጽታን የቀየረና የዜጎችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ያሳለጠ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅ፣ እንደሀገር ግንባታቸው የተጀመሩ የማዳበሪያ ፋብሪካ ጨምሮ ግዙፍ ፕሮጀክቶች በሀገር ኢኮኖሚ እድገት ላይ የሚኖራቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑን አመልክተዋል ።
እንደሀገር የተጀመሩ የልማት ስራዎች የኢትዮጵያን የከፍታ ጉዞ የሚያሳዩ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ ሌላዋ የሀዋሳ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ሙዳይ ደመቀ ናቸው።
ሀገራዊ የልማት ስራዎች የዜጎችን በሀገር ሰርቶ የመለወጥ እድል ያሰፉና ትውልድን የሚየሻገሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የጂንካ ከተማ ነዋሪ አቶ ዳኜ ዮሴፍም፤ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎች የኢትዮጵያን ከፍታ የሚያረጋግጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የባሕር በርን ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝና ሌሎች ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች እንዲሳኩ ከመንግስት ጎን በመሆን የድርሻዬን እወጣለሁ ያሉት ደግሞ የከተማው ነዋሪ አቶ ጋሻው ገላው ናቸው።