ቀጥታ፡

እየተከናወነ ባለው የሰላም ግንባታ ላይ ተሳትፏችንን ይበልጥ እናጠናክራለን - የባሕርዳር ወጣቶችና ሴቶች

ባሕር ዳር፤ ጥቅምት 21/2018(ኢዜአ)፡- በከተማው እየተከናወነ በሚገኘው የሰላም ግንባታና የልማት ተግባራት ላይ ተሳትፏቸውን ይበልጥ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የባሕርዳር ከተማ ወጣቶችና ሴቶች ተናገሩ።

የከተማው ወጣቶችና ሴቶች በሰላም ማፅናት ዙሪያ ዛሬ በባሕርዳር ከተማ ተወያይተዋል።

የውይይቱ ተሳታፊ ትዕግስት አባቡ በሰጠችው አስተያየት፤ መንግስት ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶችን በአጭር ጊዜ አጠናቆ ለአገልግሎት በማብቃት የሚደነቅ ተግባራትን እያከናወነ ነው ብላለች።

የልማት ስራዎቹ የወጣቶችንና ሴቶችን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ መሆናቸውን ጠቅሳ፤ ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አንስታለች።

ለልማት ስራዎች ተጠናክሮ መቀጠል ሰላም ወሳኝ በመሆኑ ለሰላም ግንባታ ተሳትፎዋን አጠናክራ እንደምትቀጥል ተናግራለች።

ሌላው ተሳታፊ አዲሱ ዳኘው በበኩሉ፤ ከለውጡ ወዲህ የተከናወኑ ዘርፈ ብዙ ተግባራት የወጣቶችና ሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ምቹ መደላደል የፈጠሩ ናቸው ብሏል።

እየተከናወኑ የሚገኙ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች ሃገሪቱን ወደ ላቀ የኢኮኖሚ ደረጃ የሚያሸጋገሩ እንደሆኑም ተናግሯል።

የልማት ስራዎቹ የተከናወኑት ከሰላም ግንባታ ጎን ለጎን መሆኑን ጠቅሶ፤ የልማት ተግባራትን አጠናክሮ ለማስቀጠል እንዲቻል ለዘላቂ ሰላም ግንባታ የበኩሉን እንደሚወጣ ገልጿል።


 

የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ሃላፊ ቶማስ ታምሩ፤ ከለውጡ ወዲሕ በከተማው የሕዝቡን የልማት ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ዘርፈ ብዙ ፕሮጀክቶች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

በተለይም ከተማዋን ለቱሪስቶችና ነዋሪዎች ምቹ በማድረግ በኩል የኮሪደር ልማት ስራው ለአብነት የሚጠቀስ ዋና ተግባር ነው ብለዋል።

ሌሎች የሕዝብ ፍላጎትን መሰረት ያደረጉ የልማት ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ ለዚህም የከተማው ወጣቶችና ሴቶች ድጋፍና ትብብር የጎላ መሆኑን አንስተዋል።

የተጀመሩ የልማት ስራዎች የወጣቶችንና የሴቶችን ኢኮኖሚያዊና ማሕበራዊ ተጠቃሚነት የበለጠ እንዲያሳድጉ የሰላም መፅናት ወሳኝ በመሆኑ ሴቶችና ወጣቶች የበኩላቸውን ሚና መወጣት እንዳለባቸው አፅንኦት ሰጥተዋል።


 

በከተማ አስተዳደሩ ሰላምን ከማፅናት ባሻገር ዓይን ገላጭ የሆኑ አበረታች የልማት ስራዎችን ማከናወን ተችሏል ያሉት ደግሞ የከተማ አስተዳደሩ ሴቶች፣ ሕፃናትና ማሕበራዊ ጉዳይ መምሪያ ሃላፊ ሰብለ ዘውዱ ናቸው።

ከተማዋ በተፈጥሮ ያላትን ፀጋ በኮሪደር ልማት በማጉላት ከጣና ሃይቅ ጋር ያላት ትስስር ላቅ ወዳለ ደረጃ ማሳደግ ተችሏል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም