የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ መልክአ ምድርን፣ ታሪክን፣ ህጋዊነትንና መብትን መሰረት አድርጎ ምላሽ ማግኘት ያለበት ትክክለኛ ጥያቄ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ መልክአ ምድርን፣ ታሪክን፣ ህጋዊነትንና መብትን መሰረት አድርጎ ምላሽ ማግኘት ያለበት ትክክለኛ ጥያቄ ነው
 
           ሆሳዕና፤ ጥቅምት 21/2018(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ መልክአ ምድርን፣ ታሪክን፣ ህጋዊነትንና መብትን መሰረት አድርጎ ምላሽ ማግኘት ያለበት ትክክለኛ ጥያቄ መሆኑን በዋቸሞ ዩኒቨርስቲ የሚሰሩ ምሁራን ገለፁ፡፡
ኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነቷን ለማረጋገጥ መንግሥት እየሰራ እንደሚገኝ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ መግለፃቸው ይታወሳል።
በባህር በር ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ሙሉአለም ኃይለማርያም እንደገለፁት ኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነቷን የማረጋገጥ ህጋዊም ሆነ ታሪካዊ መብት አላት።
የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት የቀጠናውን የልማት ትስስር የሚያጎለብት በመሆኑ በቀናነት ምላሽ ማግኘት እንደሚገባውም ነው የገለጹት፡፡
የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ከልማት ትስስር አልፎም የቀጣናውን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ ትልቅ ትርጉም እንዳለው ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ መልክአ ምድርን፣ ታሪክን፣ ህጋዊ መብትን መሰረት አድርጎ ምላሽ ማግኘት የሚያስችል ትክክለኛ ጥያቄ መሆኑንም አስረድተዋል።
በዩኒቨርሲቲው የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ መምህር ጌታሁን አበራ በበኩላቸው የኢትዮጵያ የባህር በር የማግኘት መብት ዓለም አቀፋዊ የህግ ድጋፍ እንዳለው ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ በጋራ ተጠቃሚነትና አብሮ በመልማት ዲፕሎማሲያዊ መርህ መመራቱንና የበርካቶች ድጋፍ ማግኘቱንም አንስተዋል።
ብሔራዊ ጥቅም ማስጠበቅ ለመንግስት ብቻ የሚተውና የአንድ ወቅት አጀንዳ ባለመሆኑ የዜጎች የነቃ ተሳትፎ ማድረግ እንደሚገባም ነው የመከሩት።
የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም በዘላቂነት አስጠብቆ ለማስቀጠል በመንግሥት የሚደረጉ ጥረቶች የተተኪውን ትውልድ ተስፋ ጭምር ያገናዘበ መሆኑንም መምህሩ ተናግረዋል።
የባህር በር ባለቤትነትን የማረጋገጥ ጥያቄው ከቀጠናው ሀገራት ጋር በትብብር ለማደግ ያለው ሚና ከፍተኛ መሆኑንም አክለዋል።