በጉራጌ ዞን በወተት ልማትና በዶሮ እርባታ ሥራ የተሰማሩ ዜጎች ውጤታማ እየሆኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በጉራጌ ዞን በወተት ልማትና በዶሮ እርባታ ሥራ የተሰማሩ ዜጎች ውጤታማ እየሆኑ ነው
 
           ወልቂጤ፤ጥቅምት 21/2018 (ኢዜአ)፡- በጉራጌ ዞን የተመቻቸላቸውን የሥራ ዕድል ተጠቅመው በወተት ልማትና በዶሮ እርባታ ሥራ የተሰማሩ ዜጎች ውጤታማ እየሆኑ መምጣታቸውን ገለጹ።
የዞኑ አስተዳደር በበኩሉ ዞኑ ያለውን የእንስሳት ሀብት በመጠቀም ዜጎችን በሌማት ትሩፋት ተሰማርተው የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ የተጀመረው ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጿል።
በዞኑ በከተማና በገጠር ይታይ የነበረው የወተት እና የእንቁላል ምርት አቅርቦት ክፍተት ለማሻሻል በተሰራው ሥራ በርካታ ወገኖች በወተት ላምና በዶሮ እርባታ ዘርፍ ተሰማርተው ተጠቃሚነታቸውን እያረጋገጡ ነው።
                
                
  
የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ከሆኑ ወጎኖች መካከል በጉራጌ ዞን እኖር ወረዳ በዶሮ እርባታ ሥራ የተሰማራቸው ወጣት ሪሃና ዲነካ በሥራዋ ስኬታማ ለውጥ እያሳየች መምጣቷን ተናግራለች።
ባለፈው ዓመት የዶሮ እርባታ ሥራዋን በ500 ዶሮዎች መጀመሯንና በአሁኑ ወቅት የዶሮዎቹ ቁጥር 6ሺህ 200 መድረሱን ትናገራለች።
ዶሮና እንቁላል ለህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ተጠቃሚ ከመሆን ባለፈ የገበያን ክፍተት በመሙላት የድርሻዋን እየተወጣች መሆኑን ተናግራለች።
የዞኑ አስተዳደር የመነሻ ብድር በማቅረብ፣ የገበያ ትስስር በመፍጠር፣ የመስሪያ ቦታ በማመቻቸና እንቁላል ማመላለሻ መኪና በመመደብ ድጋፍ እያደረገላት እንደሆነ ጠቅሳ፣ ለዚህም አስተዳደሩን አመስግናለች።
በአሁኑ ወቅትም ከራሷ ባለፈ ከ30 በላይ ለሚሆኑ ሰዎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል ለመፍጠር መቻሏን ገልጻለች።
በገራጌ ዞን በእምድብር ከተማ በወተት አቅርቦት ዘርፍ የተሰማሩት አቶ ደንድር ገጎ ከራሳቸው ባለፈ ሌሎችን ተጠቃሚ እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።
                
                
  
የከተማ አስተዳደሩ ባመቻቸላቸው ከ700 ካሬ በላይ መሬት በወተት ላም እርባታ ሥራ ተሰማርተው ለማህበረሰቡ የወተት ምርታቸውን በማቅረብ ተጠቃሚ እየሆኑ መምጣታቸውን አስረድተዋል፡፡
በዚህም ልጆቻቸውን በተሻለ ትምህርት ቤት ለማስተማርና የራሳቸውን መኖሪያ ቤት ለመገንባት እንደቻሉ ገልጸው፣ በቀጣይ ሥራቸውን አስፍተው ለመስራት ማቀዳቸውን ተናግረዋል፡፡
                
                
  
ሌላኛው የእምድብር ከተማ ነዋሪ ወጣት አበዱልሃኪም ሙራድ በበኩሉ ባለፈው በጀት ዓመት በተመቻቸለት የ200 ሺህ ብር መነሻ ካፒታል እና መስሪያ ቦታ የአንድ ቀን የዶሮ ጫጩት ተረክቦ በ45 ቀናቸው አውጥቶ የመሸጥ ሥራ መጀመሩንና በዚህም ውጤታማ እየሆነ መምጣቱን ተናግሯል።
                
                
  
የጉራጌ ዞን ግብርና መምሪያ ምክትልና የእንስሳት ዘርፍ ሃላፊ አቶ መሃመድ ሙደሲር በበኩላቸው እንዳሉት በዞኑ በሌማት ትሩፋት መርሀግብር በወተትና በዶሮ ልማት ዘርፍ የተሰማሩ ዜጎች ተጠቃሚ እየሆኑ መጥተዋል።
በዘርፉ የተሰማሩ ዜጎች ከመነሻ ካፒታልና ከመስሪያ ቦታ ባለፈ በሚያገኙት ሙያዊ ስልጠና ድጋፍ ታግዘው ምርታማ እየሆኑ መምጣታቸውን ጠቅሰው፣ በሚያመርቱት ምርት በአጭር ጊዜ ውስጥ ገበያን ከማረጋጋት ባለፈ ለበርካቶች የሥራ ዕድል መፍጠር ችለዋል ብለዋል።
ለዘርፉ በተሰጠው ትኩረት የወተት እና የእንቁላል አቅርቦት እጥረት ችግር እየተፈታ መምጣቱን ጠቁመው ለዜጎች የሥራ ዕድሎችን የማስፋት ስራ በቅንጅት እየተከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል ።
                
                
  
የጉራጌ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ በበኩላቸው በዞኑ በሌማት ትሩፋት በወተትና ዶሮ ምርት ሥራ የተሰማሩ ዜጎች ተጠቃሚነታቸውን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር በክላስተር እንዲሰሩ የማድረግ ስራ እየተመቻቸ መሆኑን ተናግረዋል ።
በተጨማሪም የተሻሻለ ዝርያ ያላቸው እንስሳት እንዲጠቀሙ፣ የመኖ አጠቃቀማቸውን እንዲያሻሽሉና ለእንስሳት ጤና አጠባበቅ ትኩረት እንዲሰጡ ድጋፍና ክትትል እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በዘርፉ ዜጎችን ተሳታፊና ተጠቃሚ ለመድረግ የተጀመረው ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።