ቀጥታ፡

የአካባቢያችንን ሰላም በመጠበቅ የልማት ተግባራት እንዲሳኩ የበኩላችንን እንወጣለን -ወጣቶች

ደሴ/ወልድያ/ ሰቆጣ፤ ጥቅምት 21/2018(ኢዜአ)፡- የአካባቢያቸውን ሰላም በዘላቂነት በማስጠበቅ  የልማት ተግባራት  ይበልጥ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የበኩላቸውን እንደሚወጡ በአማራ ክልል ወጣቶች ገለጹ።

"ሰላም ለሁሉም፣ ሁሉም ለሰላም" በሚል መሪ ሃሳብ   ወጣቶች የተሳተፉባቸው  የውይይት መድረኮች በደሴ፣ ወልዲያና ሰቆጣ ከተሞች ዛሬ ተካሂደዋል። 

ከደሴው መድረክ ተሳታፊዎች ውስጥ ወጣት ከድር የሱፍ በሰጠው አስተያየት፤  መንግስት ሰላምን ከማፅናት ጎን ለጎን የሚያካሂዳቸው ግዙፍ ፕሮጀክቶች ለወጣቶችና ለቀጣዩ ትውልድም ተስፋ የሰጡ ናቸው ብሏል።

ፕሮጀክቶቹ የሀገሪቱን እድገት በማፋጠን  መሰረታዊ ለወጥ  የሚያመጡ መሆናቸውን ጠቅሶ፤ ከሌሎች ወጣቶች ጋር በመተባበር ሰላም በማስጠበቅ ለአካባቢው  ልማት ብሎም  ለሀገራዊ ፕሮጀክቶች ስኬታማነት የበኩሉን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን ገልጿል። 

ሌላዋ የመድረኩ ተሳታፊ ወጣት ቤተልሔም ፈንታው  በበኩሏ፣ የማዳበሪያ፣ የጋዝ፣ ዓለም አቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያና ሌሎች ፕሮጀክቶች መገንባት ለመጪው ትውልድ ትልቅ ተስፋ የሰነቁ ናቸው ብላለች።

በዚህ ሂደት ፕሮጀክቶቹ ተሳክተው የሀገራችንን ብልጽግና ለማረጋገጥ የድርሻችንን ለመወጣት ቁርጠኛ ነን፤ ከፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጅት ሰላማችንን ለማጽናት የጀመርነውን ስራ እናስቀጥላለን ብላለች።


 

የደሴ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ተወካይና የሕዝብ ግንኙነት ምክትል አማካሪ አቶ አወል አህመድ በበኩላቸው፤  የከተማውን ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ ከወጣቱ ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።

የወል ትርክትን በማስፈን ሕብረብሔራዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ወጣቶች የጀመሩትን የነቃ ተሳትፎ አጠናክረው እንዲቀጥሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።


 

በተመሳሳይ በወልዲያው መድረክ ከተሳተፉት መካከል ወጣት አቤል አያሌው፤  የአካባቢያቸውን ሰላም በዘላቂነት በማስጠበቅ  ልማት ይበልጥ እንዲጠናከር  የድርሻችንን ለመወጣት መንቀሳቀስ አለብን ብሏል። 

ሰላምን በማፅናት የአካባቢውና  ሀገራዊ ተስፋ ሰጪ የልማት ተግባራት  ከፍጻሜ እንዲደርሱ በጋራ መነሳት አለብን ያለው ደግሞ ወጣት ኃይለማሪያም ስዩም ነው።

የወልድያ ከተማ አስተዳደር ስራና ስልጠና መምሪያ ሀላፊ አቶ መላኩ ዓለሙ፤  ጽንፈኛ  ቡድኑ የባዕዳን ተላላኪ በመሆን ታሪክ የማይረሳው አፍራሽ ድርጊት ለመፈፀም ቢሞክርም በፀጥታ ሀይሉ እየመከነበት በመበታተን ላይ መሆኑን አብራርተዋል።

ሰላምን በዘላቂት አፅንቶ ለማስቀጠል በሚደረገው ጥረት ወጣቶች ግንባር ቀደም ተዋናይ መሆን እንዳለባቸው  አሳስበዋል።


 

በሌላ በኩል በሰቆጣው ውይይት የተሳተፈው  ወጣት ጥላሁን አበበ፤  መንግስት ችግሮች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ እያደረገ ያለው ጥረት እንደግፋለን ብሏል።

ሌላው ተሳታፊ ወጣት አስፋው ገብረ መድህን በበኩሉ፤ ለሰላም መስፈን እኛም ከመንግስት ጎን ተሰልፈን የበኩላችንን ሚና እንወጣለን ሲሉ ገልጿል።

የሰቆጣ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ጌትነት እሸቱ በበኩላቸው፤  በአካባቢ የሰፈነውን ሰላም አስጠብቆ በዘላቂነት ለማስቀጠል  ወጣቶች ብሎም የፀጥታ አካላት እያደረጉት ያለው ተግባር የሚደነቅ መሆኑን ተናግረዋል። 

ሀገራችን ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስጠበቅ የሚያስችሉ  ስራዎች ላይ አተኩራለች ያሉት አቶ ጌትነት፤  በቀጣናው  ያላትን ተሰሚነት ለማጠናከር ወጣቶች ሚናቸውን እንዲወጡ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በከተሞቹ በተካሄደው የውይይት መድረኮች  የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ ወጣቶችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም