ቀጥታ፡

መንግስት ለእግር ኳስ ስፖርት የሰጠው ትኩረት ውጤታማነትን ለማሻሻል መነሳሳትን የሚፈጥር ነው 

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 21/2018 (ኢዜአ)፡-መንግስት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፎካካሪ የእግር ኳስ ቡድን ለመገንባት የሰጠው ትኩረት ውጤታማነትን ለማሻሻል መነሳሳት የሚፈጥር ነው ሲሉ የእግር ኳስ ስፖርት አመራሮች ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡት ማብራሪያ ካነሷቸው ጉዳዮች መካከል የኢትዮጵያ እግር ኳስ ይገኝበታል።

በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ እግር ኳስ በተፈለገው ደረጃ አለማደጉና ብሔራዊ ቡድኑ የአፍሪካ ዋንጫ ላይ አለመሳተፉ ብዙዎችን እንደሚያስቆጭ ተናግረዋል።

መንግስት ይህን ቁጭት ለመቀየር ለእግር ኳስ እድገት በርካታ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸው፤ ለአብነትም ባለፉት አመታት ከ1 ሺህ በላይ ትናንሽ ስታዲየሞች መገንባታቸውን አንስተዋል።

የተገነቡት ሜዳዎች ብቁ ታዳጊዎችን ለማፍራት ትልቅ ሚና እንደሚጫቱ ገልጸው ከአስር አመት በኋላ ብቁ የእግር ኳስ ተጨዋቾች ማፍራት እንደሚቻል በማብራሪያቸው አስታውቀዋል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የእግር ኳስ ስፖርት አመራሮች መንግስት በተለይ ለእግር ኳስ የሰጠው ትኩረት ከዚህ ቀደም ያልታየና ይበልጥ የሚያነሳሳ መሆኑን ተናግረዋል።

የአርሲ ነገሌ እግር ኳስ ክለብ ስራ አስኪያጅ ጌታነህ ታደሰ ፤ መንግስት ለእግር ኳስ ስፖርት እድገት ወሳኝ የሚባሉ መሰረተ ልማቶችንና  ስታዲየሞችን ገንብቷል ፤ እየገነባም ይገኛል ብለዋል። 


 

መሠረተ ልማቶቹ በተለይ ታዳጊዎችን በማፍራት ብቁና ተፎካካሪ ብሔራዊ ቡድን ለመገንባት ትልቅ ፋይዳ እንዳላቸው ጠቅሰዋል።

የባቱ እግር ኳስ ስፖርት ክለብ ፕሬዝዳንት ተስፋዬ ኤዳዎ መንግስት እግር ኳሱን ለማሳደግ የጀመረው ተግባር ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ትንሳኤ የጎላ ሚና አለው ብለዋል። 


 

በተለይ ታዳጊዎችን መሠረት በማድረግ የተገነቡ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችና ሌሎች ተግባራት ለእግር ኳስ እድገት ጠንካራ  መሰረት የሚጥሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የሲዳማ ቡና እግር ኳስ ስፖርት ክለብ  ስራ አስኪያጅ ከነዓን በለጠ መንግስት ለዘርፉ የሰጠው ትኩረት ውጤታማ ቡድን ለመገንባት ትልቅ መነሳሳት የሚፈጥር መሆኑን አስታውቀዋል፡፡


 

ታዳጊዎች ላይ መስራት ለእግር ኳስ እድገት ወሳኝ በመሆኑ ክለቦች ታዳጊዎችን ወደ ዋናው ቡድን ማሳደግ ላይ በትኩረት መንቀሳቀስ አለባቸው ሲሉ ተናግረዋል ።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ባህሩ ጥላሁን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በእግር ኳሱ ዙሪያ ያስተላለፉት መልዕክት ትልቅ ኃላፊነት እንዳለብን የሚያመላክት ነው ብለዋል። 


 

በቀጣይ ተፎካካሪና ውጤታማ ቡድን ለመገንባት መንግስት የፈጠረውን ምቹ ሁኔታ ለመጠቀም ፌዴሬሽኑ በትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያን እግር ኳስ ውጤታማ ለማድረግ ሁሉም በእኔነት ስሜት በጋራ መረባረብ አለበት ሲሉ ባለሙያዎቹ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም