የወጣቶችን የፈጠራ ሃሳብ ወደተግባር የሚቀይር የፋይናንስ አቅርቦት አሰራር መዘርጋቱ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን ለማፋጠን ጉልህ ጠቀሜታ አለው - ኢዜአ አማርኛ
የወጣቶችን የፈጠራ ሃሳብ ወደተግባር የሚቀይር የፋይናንስ አቅርቦት አሰራር መዘርጋቱ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን ለማፋጠን ጉልህ ጠቀሜታ አለው
 
           አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 21/2018 (ኢዜአ)፡-የወጣቶችን የፈጠራ ሃሳብ ወደተግባር የሚቀይር የፋይናንስ አቅርቦት አሰራር መዘርጋቱ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን ለማፋጠን ጉልህ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ተገለጸ።
የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማሳለጥ ወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል የሚፈጠርለትን የሥራ ዕድል ከክህሎቱ የሚያገናኝ ምቹ አሰራር ሥርዓት ምኅዳር መዘርጋት አስፈላጊ መሆኑ እሙን ነው።
ይህም ወጣቶች ክህሎታቸውን በመጠቀም በሚፈጠርላቸው የሥራ ዕድል ለሀገር ዕድገትና ከፍታ ችግር ፈቺ ስኬቶችን እንዲያስመዘግቡ ጉልህ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል፤ ከግማሽ በላይ የሚሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ ወጣት መሆኑ ለሀገር ዕድገትና ብልጽግና ከፍተኛ አቅም እንደሆነ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የልማት አቅም የሆነውን ወጣት ኃይል የሥራ ዕድል ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ስኬት እየተመዘገበ ቢሆንም ቀጣይነት ያላቸው ስራዎችን ማከናወን እንደሚጠይቅ ተናግረዋል።
የወጣቶችን በክህሎት የታገዘ ሥራ ፈጣሪነት አቅም ለማሳደግ የሚከናወኑ ተግባራትም በሁሉም መመዘኛ መሰናክሎችን ማለፍ እንደሚጠይቅ አስረድተዋል።
በዚህም የለውጡ መንግስት ወጣቶች በተለያዩ መስኮች በሚፈጠርላቸው የሥራ ዕድል ለሀገር ልማትና ዕድገት የድርሻቸውን የሚወጡበትን ምቹ ምኅዳር መፍጠር እንደቻለ ገልጸዋል።
በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት የዜጎችን የሥራ ዕድል አማራጭ ተጠቃሚነትን ለማስፋትም የተቀረጹ የአሰራርና የሕግ ማዕቀፎች ውጤት እያስመዘገቡ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ወጣቶች የፈጠራ ሃሳባቸውን ወደተግባር ለመቀየር የሚያጋጥማቸውን የፋይናንስ አቅርቦት እጥረት ለመቅረፍም የወጣቶች የኢንቨስትመንት ባንክ ለማቋቋም ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል።
የወጣቶች የኢንቨስትመንት ባንክም በኢትዮጵያ የገበያ ሥርዓት የተመዘገቡ ኢንተርፕርነሮች የሚያቀርቡት የሥራ አዋጭነት ተጠንቶ ያለምንም ማስያዣ የብድር አገልግሎት የሚያገኙበት መሆኑን አስታውቀዋል።
የወጣቶች የሥራ ዕድል ተጠቃሚነት ዕድገት እያስመዘገበ ነው ያሉት ሚኒስትሯ በተያዘው በጀት ዓመትም ለአምስት ሚሊዮን ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር የሚያስችሉ ሥራዎች እየተሰሩ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የምጣኔ ሃብት ምሁሩ ሞላ አለማየሁ (ዶ/ር)፤ መንግስት ዜጎች የሥራ ዕድል የሚያገኙበትን ምቹ የአሰራር ምኅዳር የመፍጠር ኃላፊነት አለበት ብለዋል።
                
                
  
በዚህም ሃሳብ ያላቸውን ወጣቶች ክህሎታቸውን ወደ ተግባር የሚቀይሩበትን የፋይናንስ አቅርቦት ለማሻሻል የተፈጠሩ የአሰራር ሥርዓቶች የሥራ ዕድል ፈጠራን ለማስፋት ጉልህ ፋይዳ እንደሚኖራቸው ገልጸዋል።
ይህም ወጣቶች የፈጠራ ሀሳባቸውን ወደ ተግባር በመቀየር ተጨማሪ የሥራ ዕድል አቅሞችን በማስፋት በሀገራዊ የኢኮኖሚ እድገት ላይ አዎንታዊ ሚና ማበርከት እንደሚያስችል አስረድተዋል።
በቅርቡም የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ትብብር የወጣቶች የኢንቨስትመንት ባንክ ማቋቋም የሚያስችል ሥምምነት መፈራረማቸው ይታወሳል።