አስተማማኝ እና ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ የኃይማኖት ተቋማት እየተወጡ ያለውን ሚና ማጠናከር ወሳኝ ነው - ኢዜአ አማርኛ
አስተማማኝ እና ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ የኃይማኖት ተቋማት እየተወጡ ያለውን ሚና ማጠናከር ወሳኝ ነው
 
           አርባ ምንጭ፤ ጥቅምት 21/2018 (ኢዜአ)፡-አስተማማኝና ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ የኃይማኖት ተቋማት እየተወጡ ያለውን ሚና ማጠናከር ወሳኝ መሆኑን የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ፀኃፊ ሊቀ ትጉኃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ ገለጹ።
የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ህብረት ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚካሄደው ጉባኤ ቅድመ ዝግጅት ዙሪያ ዛሬ በአርባ ምንጭ ከተማ መክሯል።
                
                
  
በመድረኩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት ቀሲስ ታጋይ ታደለ፤ አስተማማኝና ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ የሃይማኖት ተቋማት ሚና መጠናከር ወሳኝ ነው ብለዋል።
''ያለ ሰላም መኖር አንችልም ሰላም ለሰው ልጆች የመጀመሪያውና ተቀዳሚ የህልውና አጀንዳ ነው'' ሲሉም ተናግረዋል።
ሀገር አቀፍ ኹነቱ የሃይማኖት ተቋማቱ ለሰላም፣ ለልማት እና ለአንድነት እንዲሁም ለሰላም እሴቶች መፅናት እያደረጉት ያለው ተግባር እንዲጎለብት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ምክትልና የሰላም እሴት ግንባታና ብዝሃነት አያያዝ ዘርፍ ኃላፊ አቶ በቀለ ሎኮርማ በበኩላቸው ክልሉን የሰላም ተምሳሌት ለማድረግ የተቀናጀ ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
                
                
  
ክልሉ ይህን ጉባኤ ለማስተናገድ በመመረጡ መደሰታቸውን ጠቅሰው ጉባኤውን በተሳካ ሁኔታ ለማካሄድ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
የአርባ ምንጭ ከተማ ከንቲባ ተወካይና የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ መስከረም ዛፉ ፤በከተማዋ የሚካሄደው 5ኛው ሀገር አቀፍ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የተሳካ እንዲሆን ከህዝብ ጋር በቅርበት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
                
                
  
የአርባ ምንጭ ከተማ ሰላምና ፀጥታ መምሪያ ኃላፊ አቶ ገበየሁ ፃራ በበኩላቸው ሰላም ለሁሉም መሠረት በመሆኑ በአካባቢው ያለው የሰላም ፀጋ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በትኩረት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
                
                
  
በጉባኤውም ሀገር አቀፍ የሃይማኖት መሪዎች፣ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች እና የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች የሚገኙ ሲሆን እንግዶችን ተቀብሎ ለማስተናገድ ሲደረጉ የነበሩ ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውንም አስታውቀዋል።
በኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ህብረት የሚዘጋጀው 5ኛው ሀገር አቀፍ ጉባኤ በመጪው ህዳር ወር በአርባ ምንጭ ከተማ ይካሄዳል።