ቀጥታ፡

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሌማት ትሩፋት መርሃግብር የእንስሳት ሀብት በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውል አድርጓል

አሶሳ፤ጥቅምት 21/2018(ኢዜአ)፦ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሌማት ትሩፋት መርሃግብር የእንስሳት ሀብት በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውል ማድረጉን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

ቢሮው የሌማት ትሩፋት ንቅናቄ  እና የእንስሳት ጤና ኤክስቴንሽን ማስጀመሪያ መድረክ በአሶሳ ከተማ አካሂዷል።

የክልሉ ግብርና ቢሮ የእንስሳት እና ዓሳ ሀብት ልማት ምክትል ኃላፊ ዶክተር ብርሃኑ ኢቲቻ በወቅቱ እንደተናገሩት፤ የሌማት ትሩፋት መርሃግብር በክልሉ የእንስሳት ሀብት በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውል አድርጓል።

በዚህም ህብረተሰቡ የተሻሻሉ የእንስሳት ዝርያዎችን በማርባት እና የእንስሳት ጤና እንዲሻሻል በማድረግ ተጠቃሚነቱ እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል።


 

የሌማት ትሩፋት መርሃግብር ከተጀመረ ወዲህ  80 የወተት፣ 89 የማር፣ 350 የዶሮ እና 33 የዓሳ መንደሮች በክልሉ መደራጀታቸውን ጠቅሰው፤ ከዚህም ህብረተሰቡ የእንስሳት ተዋጽኦ ተጠቃሚ እየሆነ መምጣቱን ገልጸዋል።

የሌማት ትሩፋት መርሃግብሩ የእንስሳት ዘርፉ እንዲነቃቃ የሚያደርጉ ተቋማት እንዲመሰረቱ ማድረጉን ገልፀው፥ በክልሉ የተቋቋመው የፈሳሽ ናይትሮጂን ማዕከልም እንስሳትን በቀላሉ ለማዳቀል ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ለአብነት አንስተዋል።

የሌማት ትሩፋት መርሃግብሩ በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች እንዲሰፋ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ምክትል ቢሮ ኃላፊው ጠቁመዋል።

በዚህ ዓመት የሚጀመረው የእንስሳት ጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራምም ህብረተሰቡ በእንስሳት ጤና ላይ ያለውን ግንዛቤ በማሳደግ ምርታማነት እንዲጨምር ያግዛል ብለዋል።

ፕርግራሙ ከህክምና ይልቅ በሽታ መከላከል ላይ የሚያተኩር በመሆኑ ወጪ ቆጣቢ እና ከእንስሳት ዘርፍ የሚጠበቀውን ምርት ለማግኘት የሚያስችል ነው ብለዋል።

በመድረኩ ላይ ከክልሉ ሁሉም ወረዳዎች የተውጣጡ የዘርፉ አመራሮች እና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም